በአንዳንድ አካባቢዎች ነዋሪዎች መብራትና ውሃ ከተቋረጠባቸው 5 አመታትን ማሳለፋቸውን ተናገሩ

ጥር ፲፯ (አሥራ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በምእራብ ጎጃም ዞን የየስማላ ከተማ ነዋሪዎች መብራት ከተቋረጠባቸው 5 አመታትን ማሳለፋቸውን፣ በሰሜን ጎንደር ሃሙሲት ከተማ ደግሞ የከተማው ነዋሪዎች የቧንቧ ውሃ ከተቋረጠባቸው 5 አመታትን ማሳለፋቸውን ዘጋቢያችን ነዋሪዎችን አነጋግሮ የላከው ዘገባ ያሳያል። ነዋሪዎቹ ችግሮቻቸው እንዲፈቱላቸው በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ሰሚ አካል አላገኙም።
በሞጣ ከተማ ደግሞ መብራት ከተቋረጠ 2 ወር ያለፈው ሲሆን፣ በቁንዝላ ከተማ ውሃ ከተቋረጠ 2 ሳምንት አልፎታል። የቁንዝላ ነዋሪዎች የጣናን ውሃ በመጠጣት ለበሽታ እየተዳረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ የስኳርና የዘይት እጥረት መከሰቱንም ነዋሪዎች ገልጸዋል።