ነሃሴ ፲፯(አስራ ሰባት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ዛሬ በአንዋር መስጂድ የጁምአ ሰላታቸውን በመስገድ ላይ የነበሩ ሙስሊም ሴቶች በፖሊስ መደብደባቸውን የ ኢሳት ወኪል ከስፍራው ዘግቧል።
በጁምአ ሰላት ላይ የነበሩት ሙስሊም ሴቶች የተደበደቡት፤ “ሶላት መስገድ የምትችሉት በግቢ ውስጥ እንጂ ከግቢ ውጪ አንጥፋችሁ አትሰግዱም” ተብለው በውጪ እንዳይሰግዱ በፖሊሶች መከልከላቸውን ተከትሎ በተፈጠረ አለመግባባት ነው።
ሙስሊም ሴቶቹ ሁልጊዜ እንደሚያደርጉት ከውጪ አንጥፈው መስገድ መጀመራቸውን የጠቆመው ወኪላችን፤ በዚህን ጊዜ የተናደዱት ፖሊሶች ሰላታቸው በመስገድ ላይ እያሉ ደብድበዋቸዋል ብሏል።
በፖሊስ ድብደባ ከደረሰባቸው መካከል ብዙዎቹ ሶላታቸውን አቋርጠው መነሳታቸውም ተመልክቷል። ከተደበደቡት ሙስሊም ሴቶች መካከል የመፈንከት አደጋ የደረሰባቸውም አሉ።
ይህ በ እንዲህ እንዳለ ከኢድ አልፊጥር በአል ቀደም ብሎ ከቤታቸው እና ከስራ ቦታቸው ታፍነው ከታሰሩት ሙስሊሞች መካከል የቢላል ራዲዮ ጋዜጠኛ ዳርሰማ ሶሪ ዛሬ በዋስ ተፈቷል። ታሳሪዎቹ ከዚህ ቀደም ፍርድ ቤት ቀርበው በተሰጣቸው ቀነ ቀጠሮ መሰረት ዛሬ ነሀሴ 17 ቀን በድጋሚ የቀረቡ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ ጋዜጠና ዳርሰማ ሶሪን ቸምሮ ሌሎች ዎስት ታሳሪዎችን በዋስ አንዲፈቱ ባዘዘው መሰረት በዋሰ ተፈተዋል። ሌላው የቢላል ራዲዮ ጋዜጠኛ ካሊድ መሃመድ እና ሌሎች ሙስሊም ታሳሪዎች በተመሣሳይ በነበራቸው ቀጠሮ መሰረት ከሰአት ቡሃላ ፍርድ ቤት ቢገኙም ፤”ችሎት አልተሟላም” ተብለው ለፊታችን ሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በተመሳሳይ ዜናም አንዳንድ የኢህአዴግ አባላት ሀይማኖት ያከራሉ የሚባሉ ሰዎችን እንዴት እንደሚከታተሉ መረጃዎችን ለኢሳት አካፍለዋል። አብዛኞቹ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች የስልክ ጥሪ መቀበያቸው ሀይማኖታዊ መዝሙር ከሆነ በአክራሪነት ተፈርጀው ክትትል ይደረግባቸዋል። ለዚሁ ስራ ተብለው የተመደቡ ሰዎች ሆን ብለው ሰዎችን የስልክ ጥሪ መቀበያ እንደሚከታተሉ እኚሁ አባላት ተናግረዋል። ክትትል የሚደረግባቸው ሙስሊሞች ብቻ ሳይሆኑ የኦርቶዶክስ እና ፕሮቴስታንት ሀይማኖት ተከታዮችም ናቸው ሲሉ እኚህ ሰልጣኞች ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ለስለላ ስራ ተብሎ የተመደቡ እና በአንድ ለአምስት የተደራጁ የታወቁ የሀይማኖት አባቶች መኖራቸውን እነዚሁ አባላት ገልጸዋል።