መስከረም ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሰሜን ጎንደር ዞን በወገራ ወረዳ አምባጊዮርጊስ ከተማ አቀርቢያ በምትገኘው አይባ ኪዳነምህረት መሳሪያቸውን ላለማስጠነቅ ትግል የጀመሩት አርሶአደሮች ፣ ከወታደሮች ጋር ተፋልመው በርካቶችን ሙትና ቁስለኛ አድርገዋል። አንዳንድ ወገኖች የሟች ወታደሮችን ቁጥር በአስራዎች ይቆጠራል ይላሉ። ኢሳት የሟች ወታደሮች ትክክለኛ አሀዝ ለማወቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ትናንት ምሽትና ዛሬ ጠዋት በርካታ ወታደሮች ወደ ወደ አካባቢው መንቀሳቀሳቸው በህዝቡና በወታደሮች መካከል የሚካሄደው ውጊያ እየሰፋ መምጣቱን የሚያመላክት ነው። በህዝቡ በኩል እስካሁን አንድ ሰው መገደሉን ለማወቅ ተችሎአል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከሁለት ሳምንት በፊት በባህርዳር ዙሪያ አንዳሳ ቀበሌ አካባቢ በወታደሮች እና በአርሶአደሮች መካከል የተደረገውን ውጊያ መርተዋል የተባሉ ሰዎችን ለመያዝ የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል። 8 የመንግስት ወታደሮች በተገደሉት በዚህ ውጊያ ተሳትፈዋል፣ ህዝቡንም መርተዋል በሚል የተጠረጠሩ አርሶአደሮችን የአካባቢው ፖሊሶች አታለው ለመያዝ ሲሞክሩ፣ አርሶአደሮቹ “እጃችንን ለእናንተ አንሰጥም፣ መሳሪያችንንም አናስረክብም፣ ይህን ከምናደርግ ተዋግተን እንሞታለን “ በማለት ሊይዙዋቸው የመጡትን ፖሊሶች መልሰዋቸዋል።
እነዚሁ አርሶአደሮች በባህርዳር ተካሄዶ የነበረውን ከፍተኛ ህዝባዊ ንቅናቄ በመደገፍ ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርጉ እንዲሁም በተቃውሞው ተሳትፈዋል የተባሉ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ወደ እስር ቤት በመሄድ ያስፈቱ ናቸው።