ግንቦት ፲፪ (አሥራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ስራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀት ከመንግስት የመስሪያ ቦታ፣ ብድርና እንዲሁም ስራዎች እንዲያገኙ በመደገፍ ራሳቸውን እንዲደጉሙ ታሳቢ ተደርጎ ስራው የተጀመረ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ሲፈተሹ የግል ተቋማት ሆነው ተገኝተዋል። አንዳንዶቹ
ለይስሙላ በወጣቶች የተደራጁ በማስመሰልና አንዳንድ ወጣቶችን በጥቅም ደልሎ በማስፈረም የተመሰረቱ ሲሆን፣በርካታ ድርጅቶች ከተመሰረቱ በሁዋላ የወሰዱትን ብድር ሳይከፍሉ ፈርሰዋል።
በአ/አ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ በከተማዋ 27 ሺ 180 አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት መኖራቸውን እነዚህም ተቋማት ከአንድ ሚሊየን በላይለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠራቸውን፣ ካፒታላቸውም ከ972 ሚሊየን ወደ 9 ቢሊየን ማደጉን ይናገራል። ለእነዚህ ተቋማት ባለፉት አመታት ወደ 8 ቢሊየን ብር የብድር ድጋፍ የተደረገ
ሲሆን ፣ አብዛኛዎቹ ማህበራት በወጣቱ ስም ገንዘቡን ተቀብለው ለግል የንግድ ድርጅታቸው ማዋላቸው ታውቋል። በድጋፉ የተጠቀሙት የስርአቱ ደጋፊዎች ብቻ መሆናቸውን ጥናቶችን ጠቅሶ ዘጋቢያችን የላከው ሪፖርት ያስረዳል።