በአቶ አለማየሁ መኮንን ላይ እንዲመሰክሩ የሃሰት ምስክሮች እየተመለመሉ ነው ተባለ

ኢሳት (መጋቢት 30 ፥ 2008)

በጂንካ ከተማ እቶ አለማየሁ መኮንንን በሽብርተኛ ፈርጆ የሚመራው ቡድን እስካሁን የሄደበት መንገድ ህገ-ወጥና በማሰረጃ ያልተደገፈ በመሆኑ በፈጠራ ውንጀላ የሃሰት ምስክሮችን ለማዘጋጀት እየተሯሯጠ መሆኑን የውስጥ አዋቂ ምንጮች ለኢሳት አድርሰዋል።

ለዚሁ ውንጀላ ይረዳቸው ዘንድ እቶ አለማየሁ ከመያዛቸው በፊት ሃሙስ ዕለት ምሽት በከተማው ውስጥ ቦንብ መፈንዳቱን እንደመነሻ በስፋት እያስወራ መሆኑን ምንጮቹ አስታውሰው፣ በገንዘብና ጥቅማ-ጥቅሞች የሃሰት ምስክሮች እየተመለመሉ ያሉት በከተማው አውቶቡስ መናኸሪያ አካባቢ ከሚሰሩ የቀን ሰራተኞች እንደሆነና፣ ምልምል የሃሰት ምስክሮች በተሰጣቸው ጥቅም ከተስማሙ አዋሳ እንደሚወሰዱና በፈለጉት ቦታ እንደሚዝናኑ፣ ከፈተኛ የገንዘብ/መነሻ ካፒታል፣ የስራ ቦታና የገበያ ትስስር ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ቃል እንደተገባላቸው ለዚህ የታጩና የተገባላቸውን ቃል ያልተቀበሉ ወገኖች ገልጸዋል።

እንደምጮቹ ገለጻ ከሆነ የሃሰት ምስሮች ከተገኙ ለቀጣዩ የሚያዚያ 4/2008 ቀጠሮ ለማቅረብ እንደታሰበ አያይዘው አስረድተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዞኑ ፖሊስ የሃሰት ምስክሮችን ቃል ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳልሆነ፣ እንዲሁም በእነ አቶ አለማየሁ እስር ጉዳይ በዞንና በአቶ አወቀ ቡድን መካከል ልዩነት እንደተፈጠረና ስምምነት ላይ ለመድረስ አለመቻሉን እነዚሁ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።

የዞኑ የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ሕብረት (ኦህዲሕ) ስራ አስፈጻሚ አባላት በእነ አቶ አለማየሁ ላይ የተፈጸመውን ህገወጥ ድርጊት የሚቃወምና በዞኑ ያሉት ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች በአሳታፊ መንገድ እንዲመረምሩ፣ በአካባቢው የግጭት አፈታት ዘዴ እንዲፈቱና ዘላቂ መፍትሄ እንዲቀመጥላቸው የሚጠይቅ ደብዳቤ ለማስገባት መወሰኑን የገለጸ ሲሆን፣ ይህ ባይሆን የተቃውሞ ሰልፍ ለመጥራት በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ መረጃ የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ሕብረት (ኦህዲህ) ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እነ አቶ አለማየሁ መኮንን ከተያዙበት ቀን ጀምሮ ሁኔታውን ከድርጅቱ መዋቅር በተጨማሪ ከተለያዩ የዞኑ ነዋሪዎች ጋር በተገናኘ መረጃዎችን ያሰባሰበ ሲሆን የተገኙ መረጃዎች ለተለያዩ የመገናኛ ብዙሃንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የድርጊቱን ህገ-ወጥነት እያስረዳና በቅርብ እየተከታተለ መሆኑን በተጨማሪም የሌሎች የተቃውሞ ፓለቲካ ድርጅቶች አጥጋቢ የአጋርነት ድጋፍ እያገኘ መሆኑን ከድርጅቱ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያስረዳል።