(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 5/2010) የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ መሪዎች በአቶ በረከት ስምኦን አማካኝነት ብአዴንን እንደገና ለመቆጣጠር በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን ምንጮች ለኢሳት ገለጹ።
ከአቶ በረከት ጋር በመሆን በብአዴን ውስጥ የሕወሃትን ጉዳይ ለማስፈጸም የተመለመሉ ግለሰቦች ማንነትም ታውቋል።
ከነዚህ ውስጥ ከፊሉ ከዚህ ቀደምም በሕወሃት አፍቃሪነት የሚታወቁና በአመራር ላይ የነበሩ መሆናቸውንም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በነሐሴ ላይ ከሚካሄደው የኢሕአዴግ ጉባኤ አስቀድሞ በሚካሄደው የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫ አፍቃሬ ሕወሃት የሆኑ ሰዎችን ለመሙላት የተያዘውን እቅድ በበላይነት የሚመሩት አቶ በረከት ስሞን መሆናቸው ተመልክቷል።
አቶ ካሳ ተክለብርሃን፣አቶ ከበደ ጫኔ፣አቶ ታደሰ ካሳ(ጥንቅሹ) እንዲሁም ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ጌታቸው አምባዬ ደግሞ በግንባር ቀደምትነት ከአቶ በረከት ስምኦን ጋር በመቆም የተልዕኮው አስፈጻሚ መሆናቸው ታውቋል።
በአሁኑ ወቅት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ፍሬሕይወት አያሌው፣በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባልደረባ የነበሩት አቶ ሙሌ ታረቀኝ የሕወሃትንና የአቶ በረከትን ተልዕኮ ለማስፈጸም ከተሰለፉት ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውንም የወጣው መረጃ ያስረዳል።
መአዛ ገብረመድህን፣ምትኩ በየነ፣ነጻነት አበራና ገነት ገብረእግዚአብሔር የተባሉ የብአዴን አባላትም የሕወሃትን ተልዕኮ በብአዴን ውስጥ ለማስፈጸም የተጀመረውን ተልዕኮ በመቀበል የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል፡፡
ብአዴንን በሕወሃት ቁጥጥር ስር ለማዋል የተጀመረውን ሒደት በማደናቀፍ ግንባር ቀደም ይሆናሉ ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎችን በተለያየ መንገድ ከሒደቱ ለማውጣት የፍትሕ ስርአቱን በመሳሪያነት ለመጠቀምም እንቅስቃሴ መጀመሩንም መረዳት ትችሏል።
በዚህ ረገድ የኮንስትራክሽን ሚኒስትርና የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑትን ዶክተር አምባቸው መኮንን ጨምሮ የተወሰኑ የብአዴን ሰዎችን በሙስናና መሰል የፈጠራ ክስ በማቀነባበር ገለል ለማድረግ እነ አቶ በረከት ስምኦን እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።
የእነ አቶ በረከት ስምኦን የመጨረሻ ግብ እነ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ከድርጅትም ሆነ ከክልል አመራርነት በማንሳት ከሕወሃት ጋር የሚስማማና የሕወሃት ተልዕኮን የሚፈጽም አመራር መሰየም እንደሆነም ምንጮች ገልጸዋል።
በሌላም በኩል የመሪነቱን መንበር ለማግኘት የብአዴን መሪዎችን ሙሉ ድጋፍ ያገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሚያዋቅሩት አዲስ ካቢኔ የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን፣የፌደራል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊን ዶክተር ነገሬ ሌንጮን ቦታ ይተካሉ ተብሎ በአንዳንድ ወገኖች በመገለጽ ላይ ነው።
ይህም የሕወሃትን ጣልቃ ገብነት የሚቃወመው የብአዴን አመራር ከክልል ባሻገር በማዕከልም ቁጥሩ እንዲጨምር ያግዛል ተብሏል።