በአቶ ሃብታሙ አያሌው ላይ በፍርድ ቤት የተጣለበት እገዳ እንዲነሳ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥሪ አቀረበ

ኢሳት (ሰኔ 24 ፥ 2008)

በፍርድ ቤት ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ እገዳ ተጥሎበት የሚገኘውና በጽኑ ህመም ላይ የሚገኘው የአንድነት ፓርት አመራር አቶ ሃብታሙ አያሌው የተጣለበት እገዳ እንዲነሳለት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥሪውን አቅረበ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ለጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በላከው የጽሁፍ መልዕክት አቶ ሃብታሙ ከሰብዓዊ መብት አንጻር እገዳው በአስቸኳይ ሊነሳለት የሚገባ እንደሆነ አመልክቷል።

በእስር ቤት ቆያታው የተለያዩ ስቃዮች በአቶ ሃብታሙ አያሌው ላይ ሲፈጸምበት መቆየቱን ያወሳው አምነስቲ ኢንተርናሽናል በማዕከላዊ የምርመራ እና የቂሊንጦ እስር ቤቶች የነበረው ቆይታው ለጤናው መታወክ ምክንያት መሆኑን አክሎ ገልጿል።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለፈው አቶ ሃብታሙ አያሌውንና ሌሎች የፖለቲካ እስርኞችን ከቀረበባቸው የሽብርተኛ ወንጀል ክስ በነጻ ቢያሰናብትም ከሳሽ አቃቢ ህግ ተከሳሾቹ ሊፈቱ አይገባም ሲል ይግባኝ ማቅረቡ ይታወሳል።

የቀረበውን ይግባኝ ተከትሎም የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከእስር የተለቀቀውን አቶ ሃብታሞ አያሌውን ከሃገር እንዳይወጣ እገዳን ጥሎ የሚገኝ ሲሆን፣ በእገዳው ምክንያት የአቶ ሃብታሙ የጤንነት ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ከቤተሰቦቹ ለመረዳት ተችሏል።

አቶ ሃብታሙ አያሌው ላይ የተጣለው እገዳ እንዲነሳ ለቀረበው ጥያቄ ፍርድ ቤት የፊታችን ማክሰኞ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ይሁንና አምነስቲ ኢንተርናሽናል አቶ ሃብታሙ ካለበት አጣዳፊ የህመም ሁኔታ እገዳው በአስቸኳይ ሊነሳለት እንደሚገባ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረበው ጥያቄ አመልክቷል።

የአቶ ሃብታሙ ህይወት እንዲተርፍ ከተፈለገ የተጣለበት እገዳ ከሰብዓዊነት አንጻር በአስቸኳይ ሊነሳ ይገባል ሲሉ በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ የአፍሪካ ቀንድ አለም አቀፍ ዘመቻ አስተባበሪ የሆኑት ሃበር ፍቃዱ ገልጸዋል።

በአንድነት ፓርት ውስጥ በማገልገል ላይ የነበሩት አቶ ሃብታሙ፣ ከግንቦት ሰባት ቡድን ጋር ግንኙነት አለህ ተብሎ ከሁለት አመት በፊት ከሌሎች የፖለቲካ አመራሮች ጋር በሽብርተኛ ወንጀል መከሰሱ ይታወሳል።

የተለያዩ የፖለቲካና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት መንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተጣለባቸውን እገዳ ማንሳት እንዳለበት የሚጠይቅ ዘመቻን እያካሄዱ እንደሆነ ታውቋል።