በአብዛኛው በቀድሞ ባለስልጣናት የተመሰረተው ራያ ቢራ ፋብሪካ በቅርቡ ወደምርት ሊገባ መሆኑ ተሰማ፡፡

ኀዳር ፲፱(አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :- በቀድሞው የመከላከያ ኢታማጆር ሹም ሌተናንት ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳይ የቦርድ ሰብሳቢነት የሚመራው ራያ ቢራ በቀድሞ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትና ህወሃትን ተጠግተው በሚነግዱ ነጋዴዎች ከፍተኛ አክስዮን የተመሰረተ መሆኑን ምንጮች ይገልጻሉ። ማይጨው ከተማ ላይ የተገነበው ፋብሪካው 600 ሚሊየን ብር የተከፈለ ካፒታል አለው።

ከራያ ቢራ አክስዮን ባለድርሻዎች መካከል   ሌተናንት ጄኔራል ጻድቃንን እና  የቀድሞ የህወሃት ታጋይና የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን የነበረው የማነ ኪዳኔ እንዲሁም  በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት የመንግስት ቃል አቀባይ የነበሩት ወ/ሮ ሶሎሜ ታደሰም ይገኙበታል።  በመካከለኛው ምስራቅ በሚያደርጉት የንግድ ስራ የሚታወቁት አቶ ዳዊት ገ/እግዚአብሔር ከራያ ቢራ አክስዮን ውስጥ 157 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ወይንም 22 በመቶ በግለሰብ ደረጃ  በመያዝ ይመራሉ። አቶ ዳዊት ከፍተኛ አክስዮን መያዛቸው ምናልባት ከእሳቸው ጀርባ የህወሃት ሰዎች እጅ ሳይኖርበት እንደማይቀር ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ይናገራሉ።

የቀድሞው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ እየሱስ ወርቅ ዛፉም የአክሲዎን ድርሻ አላቸው። ድርጅቱ 42 በመቶ የሚሆነውን አክስዮን ለቢጂአይ ኢትዮጵያ መሸጡ ይታወቃል።

ፋብሪካው በመጋቢት ወር 2010 በ58 ግለሰቦች የተመሰረተ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የአክስዮን አባላት ቁጥር ከ2ሺ በላይ አድጎአል፡፡

በቅርቡ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 279 ሚሊየን ብር ብድር የወሰደው ይህው ፋብሪካ ብድሩን በቀላሉ ያገኘው የህወሃት ከፍተኛ ባለስልጣናት የነበሩና አሁንም በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ስለተካተቱበት ነው የሚሉ አስተያየቶች ይቀርባሉ፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ የፋብሪካውን ስራ አስኪያጅ ለማግኘት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም።

በሌላ በኩል ደግሞ የህወሃት ኩባንያ የሆነው ሼባ ቆዳ ፋብሪካ ከባንክ ኤል ሲ ወይም ሌተር ኦፍ ክሬዲት ሳይከፍት በህገወጥ መንገድ ወደ ጣሊያን አገር የላካቸው በርካታ ኮንቴነር ቆዳዎች የተጠበቀውን ዋጋ ባለማግኘታቸው የድርጅቱን አመራሮች ማበሳጨቱን የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ውቅሮ ከተማ ላይ የሚገኘው የቆዳ ፋብሪካ የመንግስት ግብር ላለመክፈል ሲል በህገወጥ መንገድ ቆዳ ቢልክም፣ ጣሊያን ውስጥ ያልተጠበቀ ዋጋ እንዳጋጠመው ምንጮች ገልጸዋል። የድርጅቱ አመራሮች ገዢው ኩባንያ ባቀረበላቸው ዝቅተኛ ዋጋ ቆዳዩን ይሽጡ አይሽጡ የታወቀ ነገር የለም። የህወሃት ኩባንያዎች የመንግስት ግብር ሳይከፍሉ በመከላከያ እና በልማት ስም እቃዎችን ወደ አገር ውስጥና ወደ ውጭ እንደሚልኩ የሰባ ቆዳ ስራ አንድ ማሳያ ነው ሲሉ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ገልጸዋል።