በአብርሃ ጅራ ከተማ በቁጥጥር ስር የዋሉት የአንድነት ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ሃለፊ በህዝብ ግፊት ተለቀቁ

ነሃሴ ፲፱(አስራ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በምእራብ አርማጭሆ ዞን በአብርሃ ጅራ ከተማ ነዋሪ የሆነው የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ወጣት

አባይ ዘውዱ ዛሬ ሰኞ ጠዋት በአካባቢው ከሚገኘው የመከላከያ ካምፕ በመጡ መቶአለቃ ተስፋየ ስዩምና መቶ አለቃ ቅባቱ  ተዋጅ በተባሉ የመከላከያ  የመረጃ እና

የደህንነት ሰራተኞች ከታሰረ በሁዋላ የአካባቢው ህዝብ ባደረገው ጫና ለመፈታት ችሎአል።

ወጣት አባይ በኤርትራ ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ጋር በራዲዮ ግንኙነት አድርገሃል ብለው እንደያዙት፣ የእርሱን መያዝ ተከትሎ የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ ወታደራዊ ካምፕ

በመሄድ “ልቀቁት” ብለው ጫና በመፍጠራቸው ከሰአታት እስራት በሁዋላ ሊፈታ መቻሉን ለኢሳት ገልጿል።

ከባህርዳር ዩኒቨርስቲ በከፍተኛ ማእረግ ተመርቆ በፖለቲካ አመለካከቱ ብቻ ከስራ መቀነሱን የገለጸው አባይ ያለፉትን አራት አመታት በከፍተኛ ጫና ውስጥ ሆኖ

ማሳለፉን ተናግሯል።

በአካባቢው የሚኖሩ ሌሎች የአንድነት አባላትም በተመሳሳይ ሁኔታ ከስራ እየተቀነሱ እና እየታሰሩ መሆኑን አባይ አክሎ ገልጿል።

የዞኑ የፓርቲው ሊ/መንበር አቶ አንጋው ተገኝም በተመሳሳይ ወንጀል ተከሶ ለወራት ታስሮ መፈታቱ ይታወቃል።የህግ ባለሙያው አቶ አንጋው እንደገለጸው ያለምንም

ስራ ላለፉት አራት አመታት ደሞዝ ተከፍሎታል። ምንም ስራ ሳልሰራ የመንግስት ደሞዝ ለምን ይከፈለኛል በሚል አቤቱታ ቢያቀርብም፣ ሚስጢር ታወጣለህ፣ በሚል ምክንያት

ስራ ሊጀመር እንደማይችል እንደተነገረውና የሲቪል ሰርቪስ በፈቀደለት መሰረት ደሞዙን ያለስራ እያገኘ መሆኑን ገልጿል ።