መጋቢት ፱(ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በምእራብ አርማጭሆ በአብርሃጅራሃ ከተማ ፀጉረ ልውጥ ሽፍቶችን አስገብተዋል በተባሉ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ፍተሻ እየተደረገ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ተናግረዋል።
የከተማው ሕዝብና የአካባቢው ገበሬ በከፍተኛ ሥጋት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ በሆቴሎች በዋና ዋና መንገዶችና መተላለፊያዎች ላይ ፍትሻ እየተካሄ ነው። ነዋሪዎች ደግሞ በሚሄዱበት አካባቢ ሁሉ መታወቂያቸውን እየተጠየቁ ነው።
እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ስር የዋለ አንድም ጸጉረ ልውጥ አለመኖሩን ነዋሪዎች አክለው ገልጸዋል።
እየተደረገ ያለው ፍተሻ በከተማው ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ታዋቂ ባለሃብቶች ከ3 ቀናት በፊት አርበኞች ግንቦት7ትን መቀላለቀላቸውን ተከትሎ የተደረገ ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል።
ካለፈው ወር ጀምሮ ወደ አካባቢው ለስራ የሄዱም ሆነ በአካባቢው የሚኖሩ ወጣቶች ወደ ኤርትራ በመሄድ ተቃዋሚዎችን ልተቀላቀሉ ትችላላችሁ እየተባሉ በመታፈስ ላይ መሆናቸውን የአካባቢው ምንጮች ተናግረዋል።
በአሁኑ ጊዜ በጠረፍ ከተማዎችና በሰሜን አርማጭሆ ከፍተኛ ውጥረት ያለ ሲሆን፣ ገዢው ፓርቲ ካለፈው ወር ጀምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊቱን ወደ ስፍራው አንቀሳቅሷል።
የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በቅርቡ ወደ አካባቢው በመሄድ ህዝቡን ለማነጋገር ጥረት አድርገውነበር።