በአባይ ግድብ ግንባታ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ካሳ ስላልተከፈላቸው ተመልሰው እየሰፈሩ ነው ተባለ

ኢሳት (ግንቦት 29 ፥ 2008)

በአባይ ግድብ ግንባታ ተብሎ ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ በርካታ ነዋሪዎች የካሳ ክፍያ ስላልተፈጸመላቸው ተመልሰው እየሰፈሩ መሆኑ ተገለጸ።

የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር በበኩሉ ከቀያቸው ለተነሱት ነዋሪዎች ሊከፈላቸው ቃል የተገባላቸው ገንዘብ አለመከፈሉን አረጋግጦ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አግልግሎት ካሳውን እንዲከፍል ስምምነት መደረሱን ለፓርላማ በሰጠው ማብራሪያ አስታውቋል።

የፓርላማው አባላት በበኩላቸው በመገንባት ላይ ለሚገኘው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውሃ ያርፍበታል ተብለው ከመኖሪያ ቀያቸው የተነሱት ነዋሪዎች የሰፈሩበት ቦታ በቂ መሰረተ-ልማት ጭምር ያልተሟላለት መሆኑን በውይይት ወቅት መግለጻቸውን ከሃገር ቤት የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

ከዚሁ ግድብ ግንባታ ጋር በተገናኘ ባለፈው አመት ከ10 ሺ የሚበልጡ ነዋሪዎች ከቀያቸው እንዲነሱ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን ወደ ቀድሞ ቀያቸው የተመለሱ ሰዎች ቁጥር ግን አልታወቀም።

የመንግስት ባለስልጣናት ካሳ እንዲከፈልላቸው ቃል የተገባላቸው ነዋሪዎች በምን ምክንያት ካሳው ሳይሰጣቸው እንደቆየ ዝርዘር መረጃን ከመስጠት የተቆጠቡ ሲሆን፣ ለተነሺዎች የሚሰጠው የገንዘብ መጠንም አለመገለጹን ለመረዳት ተችሏል።

በአባይ ግድብ ግምባታ ምክንያት ግዙፍ የተባለ ሰው ሰራሽ ሃይል የሚፈጠር ሲሆን ውሃው በአጠቃላይ በ600 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው ስፍራ ላይ እንደሚተኛ የግድቡ ባለሙያዎች አስረድተዋል።

በሰው ሰራሽ መንገድ የሚፈጠረው ይኸው ሃይቅ በርካታ ተራሮች ተውጠው እንዲቀሩ የሚያደርግ ሲሆን፣ የአካባቢ ተቆርቋሪ ግለሰቦች ድርጊቱ በአእዋፋት እንዲሁም በአከባቢ ላይ ተፅዕኖን ያሳድራል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

መንግስት በበኩሉ ሰው ሰራሽ ሐይቁ የሚያርፍበት ስፍራ በአካባቢው ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ አይኖርም ሲል ማስተባበያን ሲሰጥ መቆየቱ ይታወቃል።

በመገንባት ላይ ያለው የአባይ ግድብ በአካባቢው ሊያደርስ ይችላል ተብሎ ከተሰጋው አካባቢያዊ ተፅዕኖ በተጨማሪ በወንዙ ተፋሰስ ሃገራት ላይም ተመሳሳይ ተፅዕኖን ያሳድራል ተብሎ ይነገራል።

ኢትዮጵያና ግብፅ ይህንኑ አፅዕኖ የሚያጠና አለም አቀፍ ድርጅቶች በመቅጠር ጥናት እንዲካሄድበት በቅርቡ መወሰናቸው ይታወሳል።