በአባይ ግድብ የምንጣሮ ስራ የሰሩ መለስተኛ ተቋራጮች ገንዘባቸው መዘረፉን ገለጹ ሜቴክ የተባለውን ተቋም ዋና ተጠያቂ አድርገዋል

በአባይ ግድብ የምንጣሮ ስራ የሰሩ መለስተኛ ተቋራጮች ገንዘባቸው መዘረፉን ገለጹ
ሜቴክ የተባለውን ተቋም ዋና ተጠያቂ አድርገዋል
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 25 ቀን 2010 ዓ/ም) ቅሬታ አቅራቢዎች እንደሚሉት በህወሃቱ ጄ/ል ክንፈ ዳኘው ይመራ የነበረው ሜቴክ የአባይ ግድብ ውሃ የሚተኛበትን ደን እንዲመነጥሩ ጡረታ ከወጡ የህወሃት ነባር ታጋዮች ጋር ስምምነት አድርጎ ነበር። ከሜቴክ ጋር ስምምነቱን የፈጸሙት በአቶ ጉኡሽ ካህሳይ ባለቤትነት የሚመራው ጀዲጂ ኮንስትራክሽን ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ ቤተሳሌም ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ ሙግላት ኮንስትራክሽን ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርና በአቶ ሃይላይ አብርሃ ባለቤትነት የሚመራው ግርማነሽ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኮንስተራክሽን ድርጅት ጋር ናቸው። በ2006 ዓም በነበረው ውል መሰረት ድርጅቶቹ በእያንዳንዱ ሄክታር 13 ሺ ብር ክፍያ ይፈጸምላቸዋል።
እነዚህ ማህበራት ዋና ተቋራጭ ሆነው ከሜቴክ ጋር ስምምነት ከፈጸሙ በሁዋላ፣ ተቋራጮቹ እንደገና 23 መለስተኛ ተቋራጮችን በመቅጠር ምንጠራ ሲያካሂዱ ቀይተዋል።
ይሁን እንጅ በአቶ ጉኡሽ ካህሳይ የሚመራው ጂዲጂ ኮንስትራክሽን በስሩ የቀጠራቸው መለስተኛ ተቋራጮች ስራውን ጨርሰው ያስረከቡት ቢሆንም ክፍያ ለመፈጸም ፈቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ፣ ተቋራጮች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደውታል። ፍርድ ቤቱም የከሳሾችን አቤቱታ አይቶ ጉዳዩን ከመረመረ በሁዋላ ፣ አቶ ጉኡሽ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ያለባቸውን እዳ እንዲከድሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ሜቴክ ለአቶ ጉኡሽ መክፈል ያለበት ገንዘብ ምን ያክል እንደሆነ ጥያቄ አቅርቦ የነበረ ሲሆን፣ ሜቴክም አቶ ጉኡሽ 18 ሚሊዮን ብር ያልተከፈለ ገንዘብ እንዳላቸው ጠቅሶ ለፍርድ ቤቱ መልስ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱም ሜቴክ ለአቶ ጉኡሽ ክፍያ እንዳይፈጽም ትእዛዝ የሰጠ ቢሆንም፣ ሜቴክ ትእዛዙን በመጣስ 20 ሚሊዮን 408 ሺ 85 ብር በክፍያ፣ 2 ሚሊዮን ብር ደግሞ በብድር በአጠቃላይ 22 ሚሊዮን 408 ሺ 85 ብር ለአቶ ጉኡሽ ክፍያ ፈጽሟል ።
ከሳሾች የፍርድ ቤት ውሳኔውን በመያዝ ሜቴክ ገንዘቡን እንዲከፍላቸው አቤቱታ ቢያቀርቡም፣ የሜቴክ ባለስልጣናት ግን ገንዘቡን ለአቶ ጉኡሽ መክፈላቸውንና በተቀራኒው ከአቶ ጉኡሽ 10 ሚሊዮን ብር ክፍያ እንደሚጠብቅ ገለጹ። ፍርድ ቤቱም አቶ ጉኡሽ በባንክ ያላቸውን ገንዘብ ለማወቅ ለተለያዩ ባንኮች ደብዳቤ የጻፈ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አቶ ጉኡሽ ገንዘቡን አውጥተው በባንክ ያላቸው ብር ከ200 እንደማይበል የሚያመልክት መለስ ለፍርድ ቤቱ ሰጥቷል። አቶ ጉኡሽ ገንዘቡን በፍጥነት ከባንክ ማውጣታቸውን የሚያሳይ የባንክ ሰነድ ለፍርድ ቤቱ የቀረበ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ አቶ ጉኡሽ ገንዘቡን ይክፈሉ ከማለት ውጭ ለማስገደድ አልቻለም።
መለስተኛ ተቋራጮች እንደሚሉት 120 ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ከዘረፋ በማዳናችን የተበሳጩ የሜቴክ አመራሮች፣ ሆን ብለው የራሳቸውን ሰው ለመጥቀም እና እነሱን ለመበቀል በሚል ክፍያ እንደከለከሉዋቸው ይገልጻሉ።
ዶ/ር አብይ ጎንደርን በጎበኙበት ወቅት መለስተኛ ተቋራጮች አቤቱታቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ዶ/ር አብይም ጉዳያቸውን አጣርተው መልስ እንደሚሰጡዋቸው ቃል ገብተውላቸዋል። ይሁን እንጅ እስካሁን ምንም የተወሰደ እርምጃ ባለመኖሩ ለከፍተኛ ወጪ በመዳረጋቸው ጉዳዩን ወደ ሚዲያ ለማቅረብ መገደዳቸውን ለኢሳት ገልጸዋል።