በአባይ ግድብ ዙሪያ የሚነሱ ጉዳዮችን ለማጥናት 2 ኩባንያዎች ተመረጡ

ሚያዝያ ፪(ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ግብጽ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን በቅርቡ በአባይ ውሃ አጠቃቀምና በአባይ ግድብ ዙሪያ የስምምነት መርሆዎችን በተፈራረሙት መሰረት የግድቡን ውሃ አሞላል  እንዲሁም ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ ስለሚያስከትለው

ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽኖ ጥናት የሚያደርግ ገለልተኛ ኩባንያ ለመምረጥ በተስማሙት መሰረት  የፈረንሳይ እና የሆላንድ ኩባንያዎች መመረጣቸው ታውቋል።

የፈረንሳዩ ቢአር ኤል ኢንጂነሪንግ የውሃ አሞላሉን የግድቡን ኢንጂሪንግ ስራዎች ሲያጠና የሆላንዱ ዴልታ ራይስ ደግሞ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ያጠናል። ኩባንያዎቹ በ11 ወራት ጥናታቸውን አጠቃለው የሚያቀርቡ ሲሆን፣ ጥናቱን ተከትሎ የሚቀርቡ

ማሳሳቢያዎችን ሁሉም አገሮች ለመፈጸም ቃል ገብተዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የተደረጉት ጥናቶች ግድቡ በታችኛው አገራት ላይ ጉዳት እንደማያደርሱ ማረጋገጣቸውን ስታስታውቅ ብትቆይም፣ በሁዋላ ላይ በተደረገው ድርድር አዲስ ጥናት እንዲካሄድ ፈቅዳለች።

በቅርቡ የተፈረመው ስምምነት በሁለቱም አገራት ምሁራኖች ሲተች ቆይቷል። በግብጽ አንዳንድ ምሁራንና ፖለቲከኞች ስምምነቱ እኤእ በ1959 ግብጽና ሱዳን የፈረሙትን  የግብጽን የውሃ ድርሻ የሚያረጋግጠውን ስምምነት ዋጋ የሚያሳጣ ነው በማለት ስምምነቱ ውድቅ

እንዲደረግ አስተያየት ይሰጣሉ።

በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ አንዳንድ ምሁራን ስምምነቱ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለግብጽና ሱዳን አሳልፎ ከመስጠት አልፎ ኢትዮጵያ በውሃ ብክለት ስም አላስፈላጊ ካሳ እንድትከፍል ያስገድዳታል በማለት ይተቻሉ።

ከኢትዮጵያ ታዋቂ ምሁራን መካከል ሚንጋ ነጋሽ፣ ሰይድ ሃሰን፣ ሙሃመድ ሙጨና አቡ ግርማ ስምምነቱን አንቀጽ በአንቀጽ በመገምገም በጋራ በጻፉት ጽሁፍ  አሁን ባለው የስምምነቱ ይዘት ኢትዮጵያ ስምምነቱንም መፈረም የለባትም። ስምምነቱ ለግብጽ ካሳ የሚያሰጥ፣

የግድቡን አግልገሎት የሚገድብ፣ የአባይ ገባር ወንዞችን ከስምምነቱ የማያስወጣ መሆኑና ሌሎችም ተመሳሳይ ጉዳዮች የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ በመሆኑ ማንኛውም ምክንያታዊ የሆነ መንግስት መፈረም የለበትም ሲሉ ምሁራኑ መክረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ስምምነቱን ታሪካዊ ሲሉ ማወደሳቸው ይታወሳል።