በአባይ ግድብ ተቀጥረው የሚሰሩ ከ30 በላይ የኦሮሞና አማራ ተወላጆች ታፍነው ተወሰዱ

ጥቅምት ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ከሚፈለጉት መካከል ግድቡ አካባቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቤት ስራ አስኪያጅም ይገኙበታል

ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው ጥቅምት 21 ቀን 2009 ዓም በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ የሚገኙ ከ30 በላይ የአማራና የኦሮሞ ተወላጆች ተይዘው ሲታሰሩ፣ የአካባቢው የንግድ ባንክ ዋና ስራ አስኪያጅ ሊያዙ ሲሉ አምልጠዋል። በርካታ ወታደሮች ወደ አካባቢው በመሰማራት በሜቴክ እና በሳሊኒ ውስጥ የሚሰሩ ሰዎችን አስረው ወደ አዋሽ አርባ ወስደዋቸዋል። በርካታ የግንባታው ሰራተኞች ወጣቶችም እንያዛለን በሚል ከአካባቢው ሸሽተዋል።

“ግድቡ እንዳይጠናቀቅ ታሴራላችሁ እንዲሁም መንግስትን ለመጣል በአካባቢው ለሚንቀሳቀሱ የነጻነት ሃይሎች የገንዘብ ድጋፍ ታደርጋላችሁ” በሚል ሰበብ ወጣቶች የታሰሩ ሲሆን፣ በተለያዩ ሃላፊነት ላይ የሚገኙ በአብዛኛው የመከላከያ ኢንጂነሪንግ (ሜቴክ) ሰራተኞች መያዛቸውም ታውቋል። በአሁኑ ሰአት በአካባቢው አለመረጋጋት የተፈጠረ ሲሆን፣ የሁለቱ ብሄር ተወላጆችን  ኢላማ በማድረግ አፈሳ እያካሄዱ ነው።

የግንባታው ሰራተኞች ከአንድ ወር በፊት ተቃውሞ አሰምተው ነበር።ይህንን ተከትሎ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰራተኞች ተገድለው ጫካ ውስጥ ተጥለዋል። ግንባታውን የሚጠብቁ 3 የፌደራል ወታደሮችም እንዲሁ ተገድለው ጫካ ውስጥ ተጥለው ተገኝተዋል። በሌላ በኩል በባህርዳር ከተማ በተለያዩ ቀበሌዎች ፖሊሶች ዲሽ ሲያወርዱ መዋላቸው ታውቋል።

በባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ በተለይም በጢስ ዓባይ ከተማና አካባቢው በሚካሄደው ተከታታይ ተቃውሞና ጥቃት የተደናገጠው የህውሃት አመራር በባህር ዳር ከተማ ከምንጊዜውም በላይ ወታደሮችን በማሰማራት ወከባ እየፈጠረ ይገኛል፡፡‹‹ ለወጣቱ የስራ እድል እፈጥራለሁ! ›› ‹‹ ለዚህ ሁሉ ተቃውሞ መነሻ የወጣቱ ስራ

ማጣት ነው ›› በማለት ሲቀሰቅስ ቢቆይም፣ ከነሃሴው ህዝባዊ እምቢተኝነት በኋላ በነበሩት የስራ ቀናት በተለያዩ የከተማዋ ክፍት ቦታዎች በነጻነት ሲነግዱ ይታዩ የነበሩ ወጣቶችን በማዋከብ ምንም አይነት አማራጭ ባለማዘጋጀት በመንገድ ላይ ንግድ  እንዳያካሂዱ ሲያባርር ታይቷል፡፡

የስርዓቱ ወታደሮች ማንኛውም ወጣት በመንገድ ላይ ሁለት ወይም ሶስት ሆኖ ከታየ ‹‹ ተበተኑ!! ›› በማለት በዱላ መምታትና ማንገራገር የየዕለት ከዕለት ተግባራቸው አድረገውታል፡፡በከተማዋ በየጊዜው የለውጥ ሃይሎች የሚወስዱትን እርምጃ ተከትሎ በምሽት እና በሌሊት ለሃይማኖታዊ ስራ የሚንቀሳቀሱ አባቶችን ሳይቀር በማንገላታት አንዳንዶችን በመደብደብ ሁከት በመፍጠር ላይ ነው፡፡

የህውሃት መንግስት ወታደሮች ሰብዓዊ አሰራርን በመተው ባለፈው ሳምንት ወደ በአለ እግዚአብሄር ቤተ ክርስቲያን ማህሌት ለማድረስና ለቅዳሴ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ሲጓዙ ያገኟቸውን የሃይማኖት አባት ምንም ርህራሄ ሳያሳዩ ‹‹ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለምን አያከብሩም?የመንግስትን ትዕዛዝ ጥሰዋል !!›› በማለት በከፍተኛ ሁኔታ መደብደባቸውን በአካባቢው የሚኖሩ የአይን እማኞች ተናግረዋል፡፡