በአባይ ጉዳይ ላይ ያደረኩት ምንም ስምምነት የለም ሲል የኢትዮጵያ መንግስት አስተባበለ

ኢሳት (ታህሳስ 21 ፣ 2008)

የኢትዮጵያ መንግስት ከግብፅ መንግስት ጋር የተደረሰ ምንም አይነት አዲስ ስምምነት የለም ሲል ሃሙስ አስተባበለ።

የግብፅ ባለስልጣናት በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ጋር አዲስ ስምምነት መፈረሙንና የየትኛውም ሃገር በተናጥል በግዱቡ ላይ ምንም አይነት ስራ እንዳያከናውን ውሳኔ መደረጉን በመግለጽ ላይ ናቸው።

ሁለት የፈረንሳይ አለም አቀፍ ተቋማት በግድቡ ላይ የሚያካሄዱት ጥናት እስኪጠናቀቅ ድረስ ግድቡን በውሃ የመሙላቱን ሂደት እንዳይካሄድ ፕሬዚደንት አልሲሲና በድርድሩ የተካፈሉት የመስኖ ሚኒስትሩ ሆሳም ሞግሓዚ ለጋዜጠኞች ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት በካርቱም በተደረሰው ስምምነት ምንም አይነት አዲስ ስምምነት እንደሌለ ሃሙስ አስተባብሏል። የግድቡን የውሃ ሙሌት ስራም ከግንባታው ጋር የተያያዘ በመሆኑ የውሃ አሞላሉ በዚሁ ግንባታ ሂደት የሚቀጥል እንደሆነ በሚኒስቴር ደረጃ የመንግስት ሃላፊ የሆኑት አቶ ሞቱማ መቃሳ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

የግብፅ ተደራዳሪዎች በበኩላቸው ለሶስት ቀን ተካሄዶ በነበረው ድርድር ማጠቃለያ ላይ ጥናቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ውሃ የመሙላቱ ስራ እንደማይካሄድ ስምምነት ተደርሷል በማለት ላይ ናቸው።

ከዚህም በተጨማሪ ግድቡን ለመጎብኘት የሚቻለው የግብፅና የሱዳን ባለሙያዎች ቡድን ይሁንታን በማግኘት ብቻ እንደሆነ በስምምነቱ መካተቱን ሚኒስትር ሆሳም ሞግሃዚ አክለው ገልጸዋል።

የግብጹ ፕሬዚደንት በበኩላቸው የሃገራቸው ዜጎች በግድቡ ግንባታ ስጋት እንዳያድርባቸው ተናግረዋል።