በአስከፊ እስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ታሞ ሆስፒታል ገባ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 21 ቀን 2010 ዓ/ም) በእስር ላይ የሚገኘው ታዋቂው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በደረሰበት ህመም ምክንያት ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል መወሰዱ ታውቋል። ጋዜጠኛ ተመስገን የጀርባና የወገብ ህመም እንደሚያሰቃየው ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ያሰፈረ ሲሆን፣ ሌሊቱን በእጅጉ ታሞ ማደሩን አብረውት ከታሰሩት ከእነ አቶ አንዱአለም አራጌ መስማቱን ገልጿል።
ባለፈው እሁድ በአንድ ማህበራዊ ዝግጅት ላይ የተገኙ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በአንድ ላይ ተይዘው መታሰራቸው ይታወቃል። እስረኞቹ በአስከፊ የእስር ቤት ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ ለፍርድ አልቀረቡም። የአሰሩዋቸው ፖሊሶችም፣ ከወታደራዊ እዙ ትዕዛዝ እየጠበቁ እንደሆነ ከመናገር ውጭ መፍትሄ ሊሰጡዋቸው አልቻሉም።
እስካሁን ያልተፈቱ በእስር ላይ የሚገኙ የህሊና እስረኞች በሙሉ እንዲለቀቁ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ በመካሄድ ላይ ነው። አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያነሱና የታሰሩትን በመላ እንዲለቁ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጥያቄዎች እየቀረቡላቸው ነው።