ኢሳት (ታህሳስ 26 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ መንግስትና በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ተወካዮች መካከል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዙሪያ ሲካሄዱ የቆዩ ውይይቶችን ተከትሎ ህብረቱ አመታዊ የመሪዎች ጉባዔውን በአዲስ አበባ ለማካሄድ ወሰነ።
የህብረቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ንኮሳንዛ ድላሚኒ ዙማ በሃገሪቱ ተግባራዊ ሆኖ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመሪዎች ጉባዔ ላይ የደህንነት ስጋት ይኖረዋል ሲሉ ባለፈው ወር ስጋታቸውን ገልጸው እንደነበር አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል።
ይሁንና በሁለቱ ወገኖች መካከል በተከታታይ ሲካሄዱ የቆዩ ውይይቶችን ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የመሪዎች ጉባዔ በአዋጁ ምክንያት የጸጥታ ስጋት እንደማያጋጥመው ከኢትዮጵያ በኩል ማረጋገጫ እንደተሰጠው ተነግሯል።
በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሃላፊዎችና በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ተወካዮች በኩል ተደርሷል የተባለውን ይህንኑ ስምምነት ተከትሎ ህብረቱ አመታዊ ጉባዔ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ለአባል ሃገራቱ አስታውቀዋል።
ህብረቱ የመሪዎቹ ጉባዔን አስመልክቶ ባወጣው ፕሮግራም መሰረትም 28ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ በቀጣዩ ወር መጨረሻ እንደሚካሄድ ይፋ ተደርጓል።
ህብረቱ በድረ-ገጹ ባሰራጨው መረጃ መሰረትም ከሁለት ሳምንት በኋላ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉት የአፍሪካ ሃገራት አምባሳደሮች ለልዩ የመሪዎች ጉባዔ በሚቀርበው አጀንዳ ዙሪያ ስብሰባቸው ያካሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ የተሾሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶር ወርቅነህ ገበየሁ በሃገሪቱ የነበረው አለመረጋጋት ዕልባት በማግኘቱ የመሪዎቹ ጉባዔ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንደሚከናወን ለህብረቱ ሃላፊዎች ማረጋገጫ መስጠታቸው ታውቋል።
የህብረቱ ተሰናባች ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ድላሚኒ ዙማ የመሪዎቹ ጉባዔ መካሄጃ በቀረበበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለመሪዎቹ ስብሰባ ስጋት ያሳድራል ሲሉ ስጋታቸውን አቅርበው እንደነበር ይታወሳል።
ከህብረቱ በተጨማሪ የአሜሪካ መንግስት ዜጎቹ ወደ ኢትዮጵያ ከመጓዝ እንዲቆጠቡ በቅርቡ ለሁለተኛ ጊዜ ማሳሰቢያን ማሰራጨቱ የሚታወስ ሲሆን፣ የብሪታኒያ መንግስትም ዜጎቹ ወደ ተለያዩ የአማራ ክልሎች ከመጓዝ እንዲታቀቡ አሳስቧል።
ይኸው በሃገሪቱ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የቱሪስቶች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እንዲቀንስ በማድረጉ በሃገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።