በአስመራ ለተቃውሞ የወጡ ተማሪዎች በፖሊስ ተኩስ ተበተኑ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 22/2010)በአስመራ ከተማ ለተቃውሞ የወጡ ተማሪዎች በፖሊስ ተኩስ መበተናቸው ተዘገበ።

በከተማዋ የተሰማውን ተኩስ ተከትሎ የአሜሪካ መንግስት ለዜጎቹ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ታውቋል።

የተቃውሞው መነሻ የኮሚኒቲ ትምህርት ቤቶችን ወደ ሕዝብ ትምህርት ቤት ለመቀየር ከተያዘ ዕቅድ ጋር የተገናኘ መሆኑም ተመልክቷል።

በተኩሱ የሞተም ሆነ የቆሰለ አለመኖሩ ታውቋል።

የኤርትራ መንግስት ከሶስት አመት በፊት ተግባራዊ ለማድረግ ያቀደውን የማህበረሰብ ትምህርት ቤቶችን ወደ ሕዝብ ትምህርት ቤት የመቀየር ርምጃ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩ ለተቃውሞ ምክንያት መሆኑ ታውቋል።

ከሶስት አመታት በፊት የወጣውን እቅድ ወደ ተግባር የመቀየሩ ርምጃ በአስመራ ከተማ የሚገኘውንም የሙስሊሞች ትምህርት ቤት ወደ ህዝብ ትምህርት ቤትነት የመቀየሩ ርምጃን በተመለከተ ከ10 ቀናት በፊት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ጥቅምት 15/2017 በተጠራ ስብሰባ ላይ የትምህርት ቤቱ የበላይ ጠባቂ ሐጂ ሙሳ መሀመድ ኑር የተቃውሞ ድምጽ በማሰማታቸው በማግስቱ እንዲታሰሩ ተደርጓል።

የሳቸው መታሰር ደግሞ በከተማዋ ለተቀሰቀሰው ተቃውሞ ምክንያት መሆኑን ዘገባዎች አመልክተዋል።

በሰሜናዊው የአስመራ ክፍል የሚገኘው የሙስሊሞች ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ሐጂ ሙሳ መሀመድ እንዲፈቱ በመጠየቅ ትላንት ከሰአት በኋላ የጀመሩት ተቃውሞ ለግጭቱ ምክንያት መሆኑም ታውቋል።

የከተማዋ የጸጥታ ሃይሎች ሰልፈኞቹን በዱላ ለመግታት ያደረጉት ሙከራ የድንጋይ አጸፋ ማስከተሉንም ዘገባዎች አመልክተዋል።

የጸጥታ ሃይሎቹ ከዱላ ወደ ተኩስ በመሻገር ሰልፈኛውን የበተኑ ሲሆን ይህንንም የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ተሰራጭተዋል።

በተኩሱ የቆሰለም ሆነ የሞተ አለመኖሩ የተገለጸ ሲሆን የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚ ድረገጾችም ስለደረሰው ጉዳት መረጃ የለም ማለታቸውን የተለያዩ ምንጮች ያወጡት መረጃ ያመለክታል።