በአርባ ምንጭ ከተማ የተቅማትና ትውከት ወረርሽን ተከሰተ

ኢሳት (የካቲት 29 ፥ 2008)

በደቡብ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ የአጣዳፊ ተቅማትጥና ትውከት በሽታ በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ ከ40 በላይ ሰዎች ለህክምና ሆስፒታል መግባታቸው ተገለጠ።

ታማሚዎችን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለሞት ይዳረጋል የተባለው ይኸው ወረርሽኝ ከአርባ ምንጭ ከተማ በተጨማሪ በዙሪያዋ በሚገኙ የገጠር መንደሮች ጉዳት በማድረግ ላይ መሆኑንም የክልሉ ጤና ቢሮ ማክሰኞ አስታውቀዋል።

እስካሁን ድረስ በሰው ህይወት የደረሰ ጉዳት እንደሌለ የገለጸው የጤና ቢሮም የበሽታው ምልክት የታየባቸው 45 ሰዎች በጤና ተቋማት አስቸኳይ ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ማመልከቱን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

በሽታው ወደአጎራባች አካባቢዎች ሊዛመት ይችላል የሚል ስጋት በማሳደሩም የጤና ባለሙያዎች ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ እንደሆነ ታውቋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ የበሽታው ምልክት የታየባቸውን ሰዎች ወደህክምና መጫ ተቋማት በመውሰድ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር በመደረግ ላይ ያለውን ጥረት እንዲያግዙ የክልሉ ጤና ቢሮ ጥሪውን አቅርቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በኦሮሚያና በሶማሊ ክልሎች ያለውን የድርቅ አደጋ ተከትሎ የአጣዳፊ ጠቅማት በሽታዎች በክልሎች መታየታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማክሰኞ ገልጿል።

ካለፈው ወር ጀምሮ በትንሹ 149 ሰዎች በዚሁ በሽታ የተያዙ ሲሆን፣ በሽታው ወደሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ድርጅቱ አመልክቷል።

ከውሃ እጥረት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ድርቁ እያደረሰ ያለውን ያህል ስጋት አሳድረው እንደሚገኝም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አክሎ ገልጿል።

በኦሮሚያ ክልል ሞያሌ አካባቢ ከወራት በፊት በተቀሰቀሰ ተመሳሳይ ወረርሽኝ በርካታ ሰዎች ለህመም መዳረጋቸው መዘገባችን ይታወሳል።

በስድስት ክልሎች ተከስቶ ካለው የድርቅ አደጋ ጋር ተያይዞ ሊቀሰቀሱ የሚችሉ ተላላፊ በሽታዎችን ለመቆጣጠር ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ቢያስፈልግም ከግማሽ በላይ የሚሆነው አለመገኘቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አክሎ አስታውቋል።