በአርባምንጭ ገዢው ፓርቲ የሚያሰማው የቦንድ ግዢ ቅስቀሳ ሰሚ አላገኘም

ሚያዝያ ፲፰ (አሥራ ስምንት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የከተማዋ ነዋሪዎች እንደገለጹት የአባይ ግድብ ዋንጫ ወደ ከተማው ይመጣል በሚል ህዝቡ ዋንጫውን እንዲቀበል የገንዘብ መዋጮና የቦንድ ግዢ እንዲፈጽም ቢጠየቅም፣ ከህዝቡ የተገኘው ምላሽ ዝቅተኛ ነው። ነጋዴዎች እስከ 20 ሺ ብር፣ በአነስተኛ ስራ የሚተዳደሩት ደግሞ እስከ 150 ብር እንዲከፍሉ ሲጠየቁ፣ ነዋሪዎች ግን መክፈል ካለብን በፈቃዳችን እንከፍላለን እንጅ ልንገደድ አይገባም በማለት ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል።
ነዋሪዎች የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆናቸው የአካባቢውን ባለስልጣናት ማበሳጨቱንም ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በአካባቢው ከፍተኛ ድርቅ ገብቶ በርካታ ዜጎች አለታዊ ፍጆታቸውን ለማግኘት ተስኖአቸው እንደሚገኝ የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ በተለይ በዞኑ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች እንስሳት በረሃብ ምክንያት በማለቃቸው ነዋሪዎች እንኳንስ ተጨማሪ መዋጮ ለመክፈል ነፍሳቸውን ለማቆየት የማይችሉበት ሁኔታ መፈጠሩን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
የከተማው ህዝብ ቀደም ብሎ በተለያዩ መንገዶች ሲያደርገው የነበረውን ተቃውሞ፣ ከአባይ ግድብ መዋጪ በተጨማሪ ዳሸን ቢራ ለመጠጣት ፈቃደኛ ባለመሆን እየገለጸ መሆኑን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
ዳሸን ቢራ በመላው አገሪቱ እንዳይጠጣ እቀባ ከተጣለበት በሁዋላ፣ “ባላገሩ ቢራ” በሚል ስሙን ቀይሮ ወደ አርባምንጭ መምጣቱን የተረዱት ነዋሪዎች፣ ቢራውን ለመጠጣት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሆቴሎች ቢራውን ከአከፋፋዮች ለመቀበል ተቸግረዋል። የአርባምንጭ ህዝብ የሰሜኑ የአገሪቱ ህዝብ የወሰደውን ጠንካራ አቋም ይጋራል የሚሉት ነዋሪዎች፣ የዳሻን ወይም ባላገሩ ቢራን ባለመጠጣት የተጀመረውን የገዢው ፓርቲ ምርቶችን ያለመግዛት ተቃውሞ ወደ ሌሎች ምርቶችም በማዞር ተቃውሞውን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ይላሉ።
በሰሜን ጎንደር የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ዳሸን ቢራ በደረሰበት ህዝባዊ ማእቀብ ለኪሳራ ተዳርጓል። የተለያዩ እርዳታዎች፡በመስጠት፣ ማስታወቂ በማሰራት እንዲሁም የሆቴል ባለቤቶች በግዴታ ቢራውን እንዲረከቡ በማስገደድ ድርጀቱ ራሱን ከኪሰራ ለማዳን ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።