በአርባምንጭ የሚገኘው የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ በመፍረስ ላይ ነው ተባለ

ጥር ፳፬ (ሃያ አራት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰራተኞች ለኢሳት እንደገለጹት ለአካባቢው ህዝብ የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ በቡልጋሪያና በዲሞክራቲክ ጀርመን ድጋፍ በደርግ መንግስት ተጀምሮ ፣ በ1985 ዓም የተመረቀው የአርባምንጭ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ በመፈራረስ ላይ ይገኛል። ሰራተኞች እንደሚሉት ፋብሪካው በሶስት ፈረቃ በሚሰራበት ወቀት ለ1500 ሰራተኞች የስራ እድል ፈጥሮ ነበር። ፋብሪካው ስራ እንደጀመረ ወዲያውኑ በፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ አማካኝነት ለህወሃቱ አልሜዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ እንዲሸጥ የተደረገ ሲሆን፣ አልሜዳ ፋብሪካውን እንዲሰፋ ወይም ባለበት እንዲቀጥል ከማድረግ ይልቅ ዋና ዋና የሚባሉ የመለዋወጫ እቃዎችንና ማሽነሪዎችን በማውጣት አዲግራት ወደ ሚገኘው አልሜዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ በመውሰድ ፋብሪካው እንዲዳከም አድርጎታል ሲሉ ሰራተኞች ወቀሳ ያቀርባሉ። የአልመዳን ድርጊት የተቃወሙ ሰራተኞች ተቃውሞአቸውን ለዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ከበደ አቤት ቢሉም፣ እርሳቸው ግን “ ማሽኖች ተነቀሉ ወደ ሌላ ቦታ ተወሰደ” በማለት የምታሰሙት አቤቱታ ተቀባይነት የለውም ፣ ድርጅቱ ደሞዝ እስከከፈላችሁ ድረስ የፈለገውን እርምጃ መውሰድ ይችላል” በማለት መልስ ሰጥተው ነበር። ከ1500 የፋብረካው ሰራተኞች በአሁኑ ሰአት 150 ብቻ የቀሩ ሲሆን ፣ ከ232 ማሽኖች ውስጥ ደግሞ በስራ ላይ ያሉት 15 ብቻ ናቸው።ቀሪዎቹ ተነቃቅለው መወሰዳቸውንና የተወሰኑት ደግሞ በእሳት መውደማቸውን ሰራተኞች ይገልጻሉ። የአካባቢው ነዋሪዎች በፋብሪካው መፈራረስ የተሰማቸውን ሃዘን በመግለጽ ላይ ናቸው።
የባህርዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ቀውስ ውስጥ ከገባ በሁዋላ ብአዴን በርካሽ ዋጋ እንዲገዛው ተደርጓል። በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ዋና ዋና የጨርቅ አጨርቅ ፋብሪካዎች በኢህአዴግ ኩባንያዎች ቁጥጥር ስር የሚገኙ ናቸው።