ኢሳት (ታህሳስ 29 2008)
በደቡብ ኢትዮጵያ አርባ ምንጭ ከተማ ላለፉት 5 አመታት ያህል ሲያገለግል የቆየው የአሜሪካ የሰው አልባ የስለላና የውጊያ አውሮፕላን (ድሮን) ጣቢያ መዘጋት የሃገሪቱን ግንኙነት የሚጎዳ ዕርምጃ መሆኑ ተመልክቷል። ዩ ኤስ አሜሪካ የድሮን ጣቢያው አላስፈላጊ በመሆኑ መዘጋቱን በወቅቱ ብትገልጽም፣ የኢትዮጵያ መንግስት ቃለ አቀባይ ረቡዕ በሰጡት መግለጫ የድሮን ጣቢያው በኢትዮጵያ ጥያቄ መዘጋቱን ይፋ አድርገዋል።
በዓለም-አቀፍ ደረጃ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲዎች ላይ የሚያተኩረው “ፎርየን ፖሊሲ” መጽሄት ያነጋገራቸው ኤክስፐርቶች የ”ድሮን” ጣቢያው መዘጋት የአሜሪካንንና የኢትዮጵያን መንግስታት ወዳጅነት እንደሚጎዳና እያሻከረው እንደሚሄድ የገለጹ ሲሆን፣ የአሜሪካ ባለስልጣናትም ጣቢያው በኢትዮጵያ ጥያቄ መዘጋቱን ዘግይተው አረጋግጠዋል።
ዩኤስ አሜሪካ በኢትዮጵያ አርባምንጭ ከተማ የሚገኘው የ”ድሮን” (ሰው አልባ አውሮፕላን) ጣቢያ ለቀጣዮቹ 3 አመታት እንዲያገለግል የ6.7 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት የፈረመችው ከሶስት ወራት በፊት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ዕርምጃ ድንገተኛ ለመሆኑ አመላካች ነው ተብሏል፥ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ፔንታገን በአለም-አቀፍ ደረጃ የድሮን ተሳትፎውን ከፍ ለማድረግ በወሰነበት ሁኔታ ይህ እርምጃ መከተሉ ያልተጠበቀ ነው ሲሉ ሩሲያ ቱደይ የተባለው የሩሲያ መንግስት ሚዲያ ዘግቧል።
ዩ ኤስ አሜሪካ በኢትዮጵያ የሚገኘውን የድሮን ጣቢያ የዘጋቸው በኢትዮጵያ ጥያቄ መሆኑን የተናገሩት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ጌታቸው ረዳ በጊዜ ገደብ ውስጥ በተወሰኑ ስምምነቶች ውስጥ እንዲህ ያሉ ሁኔታችዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ በመግለጽ አሜሪካም ለጉዳዩ እንግዳ እንደማትሆን አመልክተዋል።
የአሜሪካ አየር ሃይል በአፍሪካ ቀንድ ከእነ አልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያላቸው አሸባሪዎች ለመከታተልልና ለማጥቃት የሰው አልባ አውሮፕላን በኢትዮጵያ አርባምንጭ ያሰማራው ከ2011 ጀምሮ መሆኑ ታውቋል።
ስልጣን ላይ ያለው መንግስት የዩኤስ አሜሪካንን የድሮን ጣቢያ ድንገት ለመዝጋት ስለወሰነበት ሁኔታ የታወቀና የተገለጸ ነገር ባይኖርም፣ የመንግስት አጋር “አይጋ” የመሳሰሉ ሚዲያዎች ሁኔታው ከአርበኞች ግንቦት 7 እና መሰል ሃይሎች ጋር የተገናኘ ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ መንግስት አሸባሪ ብሎ ለፈረጃቸው ሃይሎች አሜሪካ ከለላ ሆና መቀጠሏ ስልጣን ላይ ያለውን ቡድን ማስቆጣቱ ተመልክቷል።
የዩኤስ አመሪካ ለመንግስት ጥያቄ ነፍጋ የድሮውን ታቢያዎች መዝጋቱ በአካባቢው ሌላ አማራጭ ሁኔታ በተሻለ ዕድል እየተገመገመች ሊሆን እንደሚችል የኢትዮጵያ ፖሊቲካ ተመልካቾች ይገልጻሉ።