ጥር ፲፯ ( አሥራ ሰባት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ ክልል በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ቆላ ሻራ በሚባለው አካባቢ ለዘመናት ይኖሩ የነበሩ አርሶአደሮች ከተማውን ለማስፋት በሚል ከመሬታቸው እንዲፈናቀሉ በመደረጉ፣ ብዙዎች አካባቢውን ጥለው ሲሰደዱ ሌሎች ደግሞ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተዳርገዋል።
ለከተማው መስፋፋት በሚል አርሶአደሮች ከፍያ ሳያገኙ መሬታቸውን እንዲለቁ መደረጉን በመቃወም አቤቱታ ቢያሰሙም “ መሬት የመንግስት ነው “ የሚል መልስ ተሰጥቷቸዋል። የመሬት ወረራው በከተማው እስከ 15 ኪሜ የሚደርስ የገጠር ቀበሌዎችን ያካተተ ነው።
እስካሁን ቦታቸው ላይ የነበሩ አርሶአደሮች፣ መሬታችን በነጻ ከምንንነጠቅ በተገኘው ዋጋ መሸጡ ያዋጣል በማለት መሬታቸውን በርካሽ ወጋ እየሸጡ በመሰደድ ላይ ናቸው። መሬታቸውን በጉልበት የተነጠቁ አርሶአደሮች ግን አሁንም ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ተዳርገው ይገኛሉ።
ቀድሞ የመንግስት የእርሻ ልማት ጣቢያ በመሆን ከፍተኛ ምርት ሲያመርት የነበረው የእርሻ ጣቢያ የህወሃት ኩባንያ ለሆነው ኢዛና እርሻ ቢሸጥም ቦታው ምርት አልባ ሆኖ አሁንም ታጥሮ መቀመጡን ነዋሪዎች ይናገራሉ። ይህ ሰፊ ቦታ ያለምርት ተቀምጦ እያለ አርሶአደሩን ከመሬቱ ማፈናቀል ተገቢ አለመሆኑን በመግልጽ፣ በዚህ በኩል የሚመለከታቸው ሁሉ ችግራቸውን ሰምተው እንዲረዷቸው አርሶአደሮች ጥያቄ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በደቡብ ኦሞ የተከሰተው ድርቅ በማጎ ብሄራዊ ፓርክ ላይ አደጋ መደቀኑ ታውቋል።በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኘው የማጎ ፓርክ በአካባቢው የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ ወደ ፓርኩ የሚገቡት በጂንካ ከተማ ምስራቅና ምዕራብ የሚገኙት ሁለቱ – አፊያና ኔሪ – ወንዞች በመድረቃቸው የማጎ ፓርክ ለችግር መጋለጡን ምንጮች ገልጸዋል።
በማጎ ፓርክ የሚገኙ የዱር አራዊት ለመጠጥ የሚጠቀሙት ከነዚህ ወንዞች ሲሆን፣ ለግጦሽ ዕጽዋትና ለአካባቢው ሥነምህዳር ሚዛን በመጠበቅ ረገድ ትልቅ ሚና ነበራቸው ፡፡ ድርቁን ተከትሎ አራዊት ግጦሽ ፍለጋ ወደ ኬንያ ለመሰደድ የተገደዱበት ሁኔታ የታየ ሲሆን አልፎም በግጦሽና ውሃ እጥረት ለሞት እየተዳረጉ መሆናቸውን የፓርኩ ሠራተኞች ይናገራሉ።
“የሃመርና በና ወጣቶች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተከትሎ የአካባቢው ደህንነትና ፀጥታ ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ እና ከወራት በፊት የቱሪስቶች መኪና በጥይት መመታት ጋር በተያያዘ ፣ እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የጎብኚዎች ቁጥር በመቀነሱ በፓርኩ እና በአራዊቱ ላይ እየደረሰ ያለው ችግር በዞኑ አስተዳደር በክልሉም ሆነ በፌደራል መንግስቱ ትኩረት አለማግኘቱን” የአካባቢው ምንጮች ይገልጻሉ።
በማሌ ፣ በበና ጸማይ ፣ በሃመርና ዳሰነች ወረዳዎች ድርቁ የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን፣ እንስሳት እያለቁ መሆናቸውን ባለፈው ታህሳስ ወር ብቻ 6 000 /ስድስት ሺህ / የቤት እንስሳት ማለቃቸውን በመስክ ሥራ ላይ ያሉ የግብርና ባለሙያዎች ያስረዳሉ ፡፡ ከጂንካ አርባምንጭ በሚወስደው መንገድና ወረዳን ከወረዳ በሚያገናኙ መንገዶች ግራና ቀኝ የሞቱ እንስሳት ማየት ብቻ ሳይሆን ሽታውም ተጓዦችን ያስቸገረ መሆኑን የገለጹት ባለሙያዎች፣ ህዝቡም‹ የዘንድሮው የተለየ ነው ፤ ሳናልቅ ድረሱልን › እያለ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡