ጥር ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ትናንት በአርባምንጭ ከተማ ኳስ ጨዋታ ለመመልከት ወደ ሜዳ የገቡ ሰዎች የአርባ ምንጭ ወጣቶች ለመከላከያ ሰራዊት እንዳይመለመሉ የሚመክር እንዲሁም ወጣቶች ለመብታቸው እንዲነሱ የሚጠይቅ ወረቀት ተበትኖ ማግኘታቸውን ለኢሳት ተናግረዋል።
በራሪ ወረቀቱ “የአገር መከላከያ ሰራዊት ምልመላ ለአገር ድንበር ጥበቃ ወይስ እናትና አባትን መግደያ?” የሚል ርእስ ያለው ሲሆን፣ መላው የአገራችን ህዝቦች በወያኔ ኢህአዴግ የከፋፍሎ መግዛት ፖሊሲ ምክንያት የአገራችን ሃብት እየተዘረፈ ነው፣ ዜጎች በአመለካከታቸው ምክንያት ይታሰራሉ፣ የሰደዳሉ፣ ይገደላሉ፤ ከባድመ ጦርነት በሁዋላ ወታደሩ በያገሩ እየዞረ የጦርነት ማብረጃ እየተደረገ ነው፣ በሞተውም ወታደር ላይ ሃብትና ንብረት እያፈረ በመሆኑ፣ ለመከላከያ ሰራዊት ምዝገባ በየቀበሌው የተለጠፈውን ማስታወቂያ ተከትሎ ማንም ወጣት እንዳይመዘገብ ወላጆችና ልጆች ቆርጠን እንነሳ።” ይላል።
ወጣቶች ጥንቃቄ እንዲወስዱ የሚመክረው ይህ በራሪ ወረቀት፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት እንዲነሳ፣ የመከላከያ ሰራዊትና ፖሊስ በህዝብ ላይ እርምጃ መውሰድ እንዲያቆሙ፣ በየትምህርት ቤት ወታደሮችን በግዳጅ ለመመልመል እቅድ ያለ በመሆኑ ወጣቱ ከአሁኑ በአንድነት ተነስቶ ሊቃወመው እንደሚገባም ይዘረዝራል። ወረቀቱ ዴንዳሾ ወጣቶች ተነሱ የሚል ጥሪ ያቀርባል።
በሌላ በኩል በደቡብ ኦሞ ዞን ዋና ከተማ ጂንካ ከህዳር 04/2009 ጀምሮ ከጊዚያዊ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ በታሰሩት ላይ ከተጠረጠሩበት የሽብር ድርጊት ጋር በተያያዘ አንዳችም መረጃና ማስረጃ ሳይገኝባቸው መቅረቱን ምንጮች ገልጸዋል። እስረኞች ለወራት በእስር ቤቱ በኩል ምግብ ሳይቀርብላቸው በመታሰራቸው፣ ቤተሰባቸውን ከሚያስተዳድሩበት የገቢ ማስገኛ ሥራቸው ውጪ በመሆናቸው፣ እንዲሁም የመንግስት ሠራተኞች ደመወዝ በመቋረጡ እነርሱና ቤተሰባቸው ለችግር በመዳረጋቸው በ3 ቀናት ውስጥ መፍትሄ እንዲሰጣቸው፣ መልስ ካላገኙ ደግሞ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ለሚገኙ ረድኤት ሰጪ ድርጅቶች የድረሱልን ጥሪ ማቅረብ እንደሚገደዱ ደብዳቤ ጽፈዋል።
የዞኑ የደህንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልዓዛር ቶይሳ እስረኞችን በተናጠል እየጠሩ ስድስት እስረኞችን ትፈታላችሁ በማለት ቅጽ እንዳስሞላቸው ፣ለቀሪዎቹ አራቱ ማለትም ለመ/ር ዓለማዬሁ መኮንን፣ ወጣት ዳዊት ታመነ፣ አቶ አባስ አብዱላሂ እና አቶ ዘሪይሁን ኢቤዞ ግን ምንም እንዳላሉዋቸው የገለጹት ምንጮች፣ ሆኖም ትፈታላችሁ ተብለው ቅጹን የሞሉትም እስከ ጥር 29 ቀን 2009 ዓም ድረስ አለመፈታታቸውን ተናግረዋል።
ደመወዛቸው ለታገደባቸው ሁለት መምህራን -መምህር ዓለማዬሁ መኮንንና እንድሪስ መናን ደመወዛቸው መያዙ አላግባብ ነው በማለት እንዲለቀቅ የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ም/ኮ/ር ሸጎሌ ሾዴ ግንባቶ ለዞኑ ትምህርት መምሪያ ደብዳቤ ጽፈዋል።
የዞኑ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ እስረኞችን በሁለት ቦታ ከፍሎ ከፊሉን በመፍታት ሌሎችን ለማቆየት ያደረገው ሙከራ በኮማንድ ፖስቱ ስምምነት ባለማግኘቱ ሁሉም በእስር ላይ እንዲቆዩ መደረጉ ታውቋል።