ጥቅምት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአርባምንጭ ከተማ ከ200 በላይ ነዋሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና 105 ሞተር ብስክሊቶችንና 8 ባጃጅ ተሽከርካሪዎችም በተመሳሳይ መልኩ ከባለንብረቶቹ ጋር መታሰራቸውን የእስራቱ ሠለባዎቹ ለኢሳት ገለጹ።
ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በአርባምንጭ ከተማ በአፈሳ የታሰሩት ግለሰቦችና ንብረቶቻቸው ለምን እንደታሰሩ እንዳልተገለጸላቸው ያስታወቁት ሰለባዎቹ፤ ከታሰሩት ውስጥ የተደበደቡ መኖራቸውም አመልክተዋል።
ተሽከርካሪዎቹ እንዲሁም አሽከርካሪዎቹ ሥለታሰሩበት ምክንያት የታወቀ ይፋ ነገር ባይኖርም፤ አንድ ባለሥልጣን ተሠድበዋል በሚል ርምጃው መወሰዱን እንደሚጠረጥሩ ኢሳት ያነጋገራቸው የአርባምንጭ ነዋሪ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ ክፍሎች በመንግስት ባለስልጣናት የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶች እንደተበራከቱ የሚነገር ሲሆን፤ በዚህ ሳምንት ዘገባችን፤ ባለፈው እሁድ በምእራብ ጎጃም ዞን፤ በሸንዲ ከተማ የትንሳኤ ምግብር ቤት ባለቤትን ጨምሮ ሁለት ወንድማማቾችና አንድ ሌላ ሰው፤ አንዲት ሴት በጉልበት ካለወሰድኩ በሚል የፌደራል ፖሊስ መገደላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
የሟቾቹ ቁጥር አምስት እንደደረሰ የተነገረ ሲሆን፤ በወቅቱ ራት ለመመገብ የመጣ ይግብረና ሰራተኛም የፌደራል ፖሊሱ በተኮሰው ጥይት እንደቆሰለ መዘገባችን ይታወሳል።