በአርባምንጭ በቅርቡ ከተፈቱት የህሊና እስረኞች መካከል የተወሰኑት ተመልሰው መታሰራቸውና ሌሎችም ማስፈራሪያ እየደረሳቸው ነው

በአርባምንጭ በቅርቡ ከተፈቱት የህሊና እስረኞች መካከል የተወሰኑት ተመልሰው መታሰራቸውና ሌሎችም ማስፈራሪያ እየደረሳቸው ነው
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 21 ቀን 2010 ዓ/ም) በተለያዩ የሽብርተኝነት ወንጀሎች ታስረው ሲሰቃዩ የነበሩ የአርባምንጭ ከተማ ወጣቶች፣ በኢትዮጵያ የተካሄደውን ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎየተፈቱ ቢሆንም፣ በአካባቢያቸው የሚገኙ የወታደራዊ እዙ ወኪሎች ነን የሚሉ እና የወረዳው ባለስልጣናት እየዛቱባቸው መሆኑ ታውቋል።
በእነ ሉሉ መሰለ መዝገብ ተከሶ በቅርቡ ከእስር የተፈታው መርደኪዮስ ሽብሩ መልሶ እንዲታሰር የተደረገ ሲሆን፣ መልካሙ ዳዲ የተባለው ሌላው በቅርብ የተፈታው እስረኛ ደግሞ በደረሰበት ድብደባ የተነሳ ወደ ወላይታ ክርስቲያን ሪፈራል ሆስፒታል ተወስዷል። በረከት ተገኔ የተባለውን በቅርቡ የተፈታውንም እስረኛ መልሰው ለማሰር እየፈለጉት ሲሆን፣ የእሱን ጉዷኛ ዳዊት የተባለውን ወጣት ደግሞ እንደደበደቡት የደረሰን መረጃ ያማለክታል።
በቅርቡ ከእስር የተፈቱት 3ቱ ያዛውንቱ የአቶ አበበ ልጆች የሆኑት ባንተወሰን አበበ፣ አየለች አበበ እና በፈቃዱ አበበ ምንም አይነት ማህበራዊ አገልግሎት እንደማያገኙ ተነግሯቸዋል። በቅርቡ ወታደራዊ እዙ የከተማውን ህዝብ በሰበሰበበት ወቅት፣ “ የአቶ አበበ ልጆች ከመንግስት ጋር አብረው መስራት አይፈልጉም፣ የአቶ አበበ ልጆች መረሸን ነበረባቸው ነገር ግን መንግስት ሆደ ሰፊ ስለሆነ በምህረት ለቋቸዋል፤ ከዚህ በሁዋላ ከእነሲህ ሰዎች ጋር የሚገናኝ ሰው እርምጃ ይወሰድበታል” የሚል ማስፈራሪያ ተናግረው ነበር።
በሌላ በኩል ደግሞ የፌደራል ፖሊስ አባል የነበረውና በድብደባ ብዛት መኮላሸቱን ልብሱን አውልቆ ለፍርድ ቤት ያሳየው አስቻለው ደሴ ጨለማ ቤት መታሰሩ ታውቋል። አስቻለው ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርቦ አላመየሁ ታከለ በተባለ ግለሰብ ምስክር ቀርቦበታል።
ምስክሩ በተደጋጋሚ ችሎት እየተገኘ መመስከሩን የተመለከቱት ጠበቃ አለልኝ፣ ምስክሩን “ በየጊዜው እየመጣህ ትመሰክራለህ አይደል?” ብለው ሲጠይቁት፣ መስካሪውም “ አዎ” በማለት አምኗል። ጠበቃውም፣ ታዲያ በየጊዜው ማዕከላዊ ውስጥ ተገኝቼ ለመርማሪዎች ቃል ሲሰጡ ሰማሁ እያልኢ ስትመሰክር መንግስት የመደበልህን ጥቅማ ጥቅም ልትገልጽ ትችላለህ?” ብለው ሲጠየቁት፣ ዳኞቹ የጠበቃውን ጥያቄ እንደማይቀበሉት ገልጸዋል። ጠበቃው “ ጥያቄያቸው በአዋጅ ቁጥር 666/2003 የተደነገገ ስለሆን ምስክሩ ሊመልሱ ይገባል” በማለት ቢከራሩም፣ ዳኞቹ በብስጭት አንቀበለም ብለዋቸዋል። “ምስክርነቱ ይበላሽብኛል’ የሚለው አቃቤ ህግ ተቃውሞ ሳያቀርብ፣ ዳኞች ተቃውሞ ማቅረባቸው በችሎቱ የተገኙትን ሁሉ አስገርሟል።