በአርባምንጭ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለዘመናት ከኖሩበት ቦታ እየተፈናቀሉ መሆኑን ገልጹ

መጋቢት ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት፣ ሃንዳዋሎ በሚባለው አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ከ1500 በላይ አባዎራዎች ከተማዋ የዛሬ 50 ዓመት ስትቆረቆር ጀምሮ ከነበሩበት ቀየ ለቃችሁ ውጡ በመባላቸው፣ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠዋል።
ነዋሪዎች እንደሚሉት ከነባር ይዞታቸው ሲነሱ አስፈላጊው ቤትና ቦታ አልተሰጣቸውም። ለምን ብለው የጠየቁ ከ10 ያላነሱ ሰዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ ነዋሪዎች ገልጸዋል። ዜጎች እየተፈናቀሉ መሬቱ ለካቢኔ አባላቱ እየተሰጠ ነው የሚሉት ነዋሪዎች፣ ጉዳዩን ለክልል ባለስልጣናት ሳይቀር ቢያመለክቱም መልስ አለገኙም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተንተርሶ ፖሊሶች ወደ አካባቢው በመሄድ ሰዎችን እያፈናቀሉና እያሰሩ ነው።
በቦንኬ ወረዳም እንደዚሁ በሺዎች የሚቆጠሩ አርሶአደሮች ከመሬታቸው እየተፈናቀሉ መሆኑን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል። ድርጊቱ ያስቆጣቸው አርሶአደሮች ለባለስልጣናት አቤቱታ ቢያቀርቡም የሚሰማቸው አላገኙም።