ኅዳር ፲፭ (አሥራ አምስት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሰሜን ጎንደር በአርማጭሆና ሌሎችም ቦታዎች በአርበኞች ግንቦት7 ሃይሎች እና በህወሃት/ኢህአዴግ ወታደሮች መካከል የሚካሄደው ጦርነት ዛሬም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን፣ የአርበኞች ግንቦት 7 አንድ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ መከበቡብ እንዳወቀ ራሱን ሰውቷል።
ቀደም ብሎ በኢህአዴግ መከላከያ ውስጥ ሲያገለግል ቆይቶ፣ በስራዊቱ ውስጥ ያለውን ዘረኝነትና በህዝቡ ላይ የሚፈጸመውን ግፍ መቋቋም ተስኖት፣ አርበኞች ግንቦት 7ትን የተቀላቀለው ሻለቃ መሳፍንት ጥጋቡ፣ ሃይሉን እየመራ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ጥሶ የገባ ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ከገባ በሁዋላ፣ ከስርዓቱ ወታደሮች ጋር ለቀናት ተዋግቷል።
በእነዚህ ውጊያዎች ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአገዛዙ ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን፣ ገዢው ፓርቲ ታንኮችንና ከባድ መሳሪያዎችን በማሰለፍ የመሸገበትን ቦታ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።በበረሃ ስሙ ገብርዬ እየተባለ የሚጠራው ሻለቃ መሳፍንት መከበቡን እንዳወቀ እጄን ለህወሃት አልሰጥም በማለት በያዘው መሳሪያ ራሱን መሰዋቱን የንቅናቄው ቃል አቀባይ ለኢሳት ተናግሯል። የመንግስት ጋዜጠኞች ዘጋቢ ፊልም ለመስራት የሻለቃ መሳፍንትን አስከሬን በተለያዩ አቅጣጫዎች እያስተኙ ቀረጻ ያካሄዱ ሲሆን፣ ጋዜጠኞች በህወሃት ወታደራዊ አዛዦች ድርጊት በመበሳጨት የተቀረጹ ፎቶግራፎችን ለኢሳት ልከዋል።
በጋይንት አውራጅ ንፋስ መውጫ ከተማ በ1965 ዓም የተወለደው ሻለቃ መሳፍንት፣ በ1978 ዓም የኢህአዴንን ሰራዊት የተቀላቀለ ሲሆን፣ ህወሃት አዲስ አበባን ሲቆጣጠር በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ አገልግሏል። በዚህን ወቅት በፈረንሳይ አገር ለ2 አመት ወታደራዊ ሳይንስ ትምህርት ተምሯል። የታገልኩት ወይም ጓደኞቼ የሞቱለት ስርዓት ለዚህ አልነበረም በማለት ከ3 አመታት በፊት ለኢሳት ቃለምልልስ የሰጠው ሻለቃ መሳፍንት፣ በግለሰብ ደረጃም ከፍተኛ ክትትል ሲደርግበት ቆይቷል
ኢትዮጵያ – “ኢትዮጵያዊ የሆነ መሪ ያስፈልጋታል” በማለት የተናገረው ሻለቃ መሳፍንት፣ በስልጣን ላይ ያለው ቡድን ኢትዮጵያዊ ደም ቢኖረውም፣ ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ የሌለው በመሆኑ፣ ሁላችንም ኢትዮጵያዊ መሪ እንዲኖረን እንታገል ሲል ጥሪ አቅርቦ ነበር። በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተሰውትን ታጋዮች ብዛትና ማንነት ለማወቅ ተጨማሪ መረጃዎች እየተሰባሰቡ በመሆኑ አሁን ለመናገር እንደማይቻል የገለጸው ቃል አቀባዩ፣ መረጃዎች እንደደረሱ በሚቀጥሉት ቀናት መግለጫ ይሰጣል ብሎአል።
በገዢው ፓርቲ በኩል የደረሰው ኪሳራ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ ታጋዮቻቸው አሁንም ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረጉ ነው ብለዋል።