በአርሲ በቆጂ ከተማ አንድ ባለሃብት የተቃዋሚ ዳጋፊ ናቸው በሚል ድርጅታቸው ተዘጋ

ጥቅምት ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢሳት የአካባቢው ወኪሎች እንደገለጹት ባለሀብቱ አቡ ታዬ የሚባለውን ሆቴላቸውን ጨምሮ 3 ሱፐር ማርኬቶች ( የገበያ ማእከሎች)፣ 6 የእቃ ማጠራቀሚያ መጋዚኖች፣ እና ሌሎች በርካታ ድርጅቶቻቸው ታሽገውባቸዋል።
ባለሀብቱ ገዢውን ፓርቲ አይደግፉም በሚል ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ግብር ሲጣልባቸው ቆይቷል። ተቃዋሚዎችን መደገፉን ትተህ ኦህዴድን ደግፍ እየተባሉ ቢዋከቡም፣ ባለሃብቱ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ችግራቸውን የሚሰማላቸው በማጣታቸው አዲስ አበባ ድረስ በመሄድ ለመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ቢያመለክቱም ጉዳያቸውን የሚሰማ በመጥፋቱ ለከፍተኛ ችግር ተዳርገው ቆይቷል። በመጨረሻ ድርጅቶቻቸው በሙሉ በመዘጋቱ መፍትሄ ማጣታቸውንና እርሳቸውም ቤተሰባቸውም ችግር ላይ መውደቃቸውን ወኪላችን ከስፍራው ዘግቧል።
በተመሳሳይ ዜናም በዚሁ ከተማ የሰማያዊ ፓርቲ አባል ናቸው የተባሉት አቶ ሲሳይን የተባሉትን ግለሰብ ካሰሩ በሁዋላ መኖሪያ ቤታቸው እንዲፈርስ በመደረጉ ቤተሰቦቻቸው ለችግር ተዳርገዋል። ሌሎች 12 ሰዎችም ታስረው የሚገኙ ሲሆን፣ ቤተሰቦች ለፍርድ ቤት አቤቱታ ቢያሰሙም የሚሰማቸው አካል ባለማግኘታቸው ፣ ጉዳያቸውን ለበላይ አካል ለማቅርብ ደክመው ተስፋ ቆርጠው መቀመጣቸውንም ይገልጻሉ።