አቶ ከበደ ተሰራ በኢትዮጵያው ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ምህረት መለቀቃቸው ተነገረ ።

 

(ኢሳት ዜና ሐምሌ- 6/2009)    በአርራጣ ብድርና በህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ተከሰው የ 25 አመት እስር ፍርደኛ የነበሩት አቶ ከበደ ተሰራ በኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ምህረት መለቀቃቸው ተነግሯል።

አቶ ከበደ ተሰራ በአንድ ወቅት በአራጣ አበዳሪነታቸው የ አለም ባንክ (ወርልድ ባንክ) የሚል ቅጽል ስም በህብረተሰቡ ወቶላቸው  እንደነበር ይታውቃል።

በፐሬዝደን ሙላቱ ምህረት የተደረገላቸው ኣቶ ከበደ ተሰራ 8 ዓመታት ከታሰሩ በኋላ 17 ዓመታት የእስር ጊዜ ሲቀራቸው መሆኑን ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል ።

አቶ ከበደ ተሰራ በአራጣ ብድርና በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ከተከሰሱ በኋላ የ25 ዓመታት እስር ሲፈረድባቸው 4 ኪሎ ቱሪስት ሆቴል አጠገብ የሰሩት ባለ ዘጠኝ ፎቅ ህንጻን መንግስት ወርሶባቸዋል።

የህንን ፎቅ የወረሰው መንግስትም በጨረታ ሂደት በ680 ሚሊዮን ብር ለንግድ ባንክ መሸጡ የታወሳል አቶ ከበደ ተሰራ ከእስር ሲወጡ የ 75 ዓመት አዛውንት መሆናቸውን ዘገባው ጨምሮ ገልጿል ። በተመሳሳይ የአራጣ ብድርና ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ተከሰው ዘብጥያ የወረዱት አቶ አየለ ዱባለ 22 ዕመታት ተፈርዶባቸው በእስር ላይ አንዳሉ መሞታቸው ይታወሳል ።አቶ አየለ ዱባለም አይ ኤም ኤፍ በሚል ቅጽል ስማቸው ያታወቁ ነበር።

አቶ ከበደ ተሰራም ሆነ አቶ አየለ ዱበለ ለበርካታ ዓመታት በአራጣ ብድርና በህገወጥ ሲታሙ ለረጅም ግዜ ሳይታሰሩ ከቆዩ በኋላ በአንድ ውቅት በድንገት መታሰራቸውን ብዙዎችን ሲያነጋግር የነበረ ጉዳይ ነው ።

ሁለቱም ፍርደኞች በታክስ ማጭበርበርም ተከሰው እንደነበር አይዘነጋም ። አቶ ከበደ ተሰራ በአሁኑ ጊዜ ለምን በፕሬዘዳንት ሙላቱ ተሾመ በምህረት ሊለቀቁ እንደቻሉ የተገለጸ ነገር የለም። የአቶ ከበደ ጠበቃ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።