ኢሳት (ሰኔ 29, 2008)
በአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ዕርቀት ላይ በሚገኘው የአምቦ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ግቢ ተመድቦ በማገልገል ላይ የነበረ አንድ የጸጥታ አባል ሁለት የፌዴራል ፖሊስ አባላትን ገድሎ ማምለጡን እማኞች ለኢሳት አስታወቁ።
አዋሮ ተብሎ በሚጠራው የዩኒቨርስቲው ካምፓስ ሰኞ በጸጥታ ባልደርባው በተፈጸመው ጥቃት ሶስት ተጨማሪ የፌዴራል ፖሊስ አባላት በጥይት ጉዳይ እንደደረሰባቸው ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የአምቦ ከተማ ነዋሪ ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።
የአፋር ብሄር ተወላጅ መሆኑ የተነገረለት የጸጥታ ባልደርባ በሙስሊም የጾም ወቅት ከስራ ምደባ ጋር በተገናኘ ከሃላፊዎቹ ጋር በተደጋጋሚ አለመግባባት ውስጥ መቆየቱንና ድርጊቱ የዚሁ መነሻ እንደሆነ ከእማኞች ለመረዳት ተችሏል።
ስሙ ለጊዜው ያልተገለጸው የጸጥታ አባል ከሃላፊዎቹ ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት ምክንያት በማድረግ ሰኞ የዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ ተኩስ መክፈቱንና ሁለት የጸጥታ ባልደርቦችን እንደገደለ ታውቋል።
ይሁንና ድርጊቱን የፈጸመው የጸጥታ ባልደባ እስከ ረቡዕ ድረስ አለመያዙን እማኞች አክለው አስረድተዋል።
ድርጊቱ የተፈጸመው የዩኒቨርስቲው የምረቃ ስነስርዓት ባካሄደ ማግስት በመሆኑ፣ አብዛኛው የዩኒቨርስቲው ተማሪ ከቅጥር ግቢው ወጥቶ እንደነበር እማኞች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስታውቀዋል።
በተኩስ ዕርምጃው ጉዳት የደረሰባቸው ሶስት የፌዴራል ፖሊስ አባላት በጸጥታ ሃይሎች ለክህምና ከአምቦ ከተማ ውጭ መወሰዳቸውን እማኞች አክለው አስታውቀዋል።