(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 16/2010) በአምቦ በተነሳው ተቃውሞ 6 ሰዎች ተገደሉ።
የአምቦ ከተማ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ጋዲሳ ደሳለኝ ለጀርመን ድምጽ ሬዲዮ የአማርኛው አገልግሎት እንደተናገሩት ግን በአጋዚ ኃይል የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 10 ነው።
ስኳር የጫኑ ተሳቢ ተሽከርካሪዎችን በማገት ወዳስቀረው የአምቦ ከተማ ህዝብ ዛሬ ጠዋት የመከላከያ ሰራዊቱንና የፌደራል ፖሊስ ሃይል ያሰማራው መንግስት በትንሹ 20 ሰዎችን ማቁሰሉንም መረጃዎች ያመለክታሉ።
አምቦ ከቀትር በኋላ ሙሉ በሙሉ በሰራዊት ቁጥጥር ስር ውላላች። ተቃውሞው በሌሎችም አካባቢዎች በመካሄድ ላይ ነው።
አምቦ ዛሬ በተኩስ ስትናወጥ፣ በተቃውሞ ስትናጥ ነው ያረፈደችው።
ስኳር ጭነው ከከተማዋ ሊወጡ የነበሩ ተሳቢ ተሽከርካሪዎችን ያገተውና ያስቀረው የአምቦ ከተማ ነዋሪ ዛሬ ጠዋት ማልዶ የጠበቀው እስከ አፍንጫው የታጠቀ የህወሀት መንግስት ሰራዊት ነበር።
ከማክሰኞ ጀምሮ የተነሳውን የህዝብ ተቃውሞ የሰራዊት ሃይል ከሌላ ቦታ በማምጣት ለማስቆምና ስኳሩን ለማስለቀቅ የተሰማራው የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ ሃይል ከአምቦ ከተማ ህዝብ የጠበቀው ጠንከር ያለ ምላሽ ነበር።
መንገዶችን በተቃጠሉ ጎማዎችና በግዙፍ የዛፍ ግንዶች በመዝጋት የሰራዊቱ ግስጋሴን ለጊዜው መግታት ትችሏል።
ዛሬ ጠዋት ሃይሉን አሰባስቦና የተዘጉ መንገዶችን በግሬደር እየጠረገ የመጣው የህወሀት ሰራዊት አምቦ ሲደርስ ህዝብ ላይ በቀጥታ መተኮስ መጀመሩን ነው የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት የገለጹት።
ስድስት ሰዎች ወዲያውኑ ሲገደሉ አምስት ሰዎች መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ሲናገሩ የአምቦ ከተማ የኮሚኒኬሽን ሃላፊ ደግሞ የተገደሉት ሰዎች አስር መሆናቸውን ለጀርመን ሬዲዮ በመግለጽ ገዳዮቹ የአጋዚ ወታደሮች ናቸው ብለዋል። አምቦ ዛሬ የጦር አውድማ መስላ ውላላችም ይላሉ ነዋሪዎች።
ጉደር፣ ጊንጪንና የአምቦ ዙሪያ መንደሮችን ያዳረሰው ተቃውሞ መነሻው ተጭኖ ሊወጣ የነበረው ስኳር ቢሆንም ህዝቡን ያነቃነው ጉዳይ የከረመ ብሶትና አጠቃላይ ምሬት መሆኑ ይነገራል።
እስከ ቀትር ድረስ በነበረው ተቃውሞ የህወሀት ሰራዊት ወደ አምቦ ከተማ መግባት አቅቶት የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ከተማዋን ሙሉ በሙሉ በመውረር በወታደራዊ ቁጥጥር ስር እንድትሆን ተደርጓል።
ስኳሩን ከጫኑት ተሳቢ ተሽከርካሪዎች ሌላ የዳንጎቴ ኩባንያ ንብረት የሆኑ ሁለት ተሽከርካሪዎች ተቃጥለው መውደማቸውንም ለማወቅ ተችሏል።
ከትላንት ጀምሮ ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆና የነበረችው አምቦ ዛሬም ትምህርት ቤቶች፣ የንግድ ቦታዎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች በሙሉ ተዘግተው ውለዋል።
የአምቦ ከተማ ዋና መንገዶች በህወሀት መንግስት ሰራዊትና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች የተሞሉ ሲሆን ከቀትር በኋላ በመንገድ ላይ የተገኘን አንድ ወጣት በጥይት ተኩሰው ማቁሰላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ተቃውሞ ከአምቦ ሌላ በወለጋ ሻምቡ ቄሌም ወለጋና በጊንጪ መካሄዱንም ለማወቅ ተችሏል።
ማምሻውን ያነጋገርነው የአምቦ ነዋሪ እንደሚለው ከተማዋ በሰራዊት ተወራለች። ህዝቡ በቁጣ ላይ ነው። ነገ ምን እንደሚሆን አይታወቅም ብሏል።