በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት የታሰሩ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በግዳጅ ወደኢትዮጵያ ሊመለሱ ነው ተባለ

ኢሳት (ሚያዚያ 6 ፥ 2008)

የተለያዩ አገራትን አቋርጠው በስደት ወደ አሜሪካ የገቡትና ፍሎሪዳ ታስረው የሚገኙ 11 ኢትዮጵያውያንን በግዳጅ ወደ አገር ቤት ለመመለስ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ተገለጸ።

በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኗል፣ ግለሰቦቹም ወደ ኢትዮጵያ ቢመለሱ ምንም አይሆኑም በሚል የአሜሪካ መንግስትን ያታለለው የኢትዮጵያ መንግስት፣ የታሳሪዎችን ዶክመንትም በራሱ ሰዎች እጅ እንዳስገባ ታውቋል። በዚሁ በፍሎሪዳ ክፍለ ግዛት ታስረው የሚገኙ 2 ኢትዮጵያውያን በቅርቡ ወደከፋ እስርቤት እንደተወሰዱም ታውቋል።

ብራዚል፣ ፔሩ፣ ኢኳዶር፣ ፓናማ፣ ሜክሲኮና ሌሎች አገሮችን አቆራርጠው አሜሪካ ከደረሱ በኋላ በፍሎሪዳ ወህኒ ቤት ታስረው ከሚገኙት 9 ኢትዮጵያውያን 7ቱ የመመለስ ሂደቱ በየትኛውም ሰዓት ላይ ሊፈጸም እንደሚችል በወህኒ ቤት ውስት ታስረው ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን አንዱ ለኢሳት ተናግሯል።

ራሱና አንድ ጓደኛው በአሜሪካ የጠየቁት የጥገኝነት ጥያቄም ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱን ለኢሳት ቃለምልልስ የሰጠው ይህ ኢትዮጵያዊ፣ የኢህአዴግ መንግስት ኢምባሲን ወክሎ የቀረበው ሰው የእስረኞችን ማንነትና የቤተሰቦቻቸውን አድራሻ በስልክ እንደጠየቃቸውም ከኢሳት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ገልጿል።

በቅርብ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ በግዳጅ ተላልፎ የተሰጠው ታሳሪ፣ ኢትዮጵያ ከደረሰ በኋላ ወዴት እንደተወሰደ የሚታወቅ ነገር አለመኖሩን እነዚሁ ታሳሪዎቹ ገልጸዋል።

እነዚህ ኢትዮጵያውን የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እንዳልጎበኛቸው ገልጸው፣ አቶ ከፍያለው የተባሉ ኢትዮጵያዊ ሰው ብቻ እየመጡ እንደሚጎበኟቸውና ምክርም እንደሚለግሷቸው ገልጸዋል። በቅርቡ ደግሞ አቶ ሙሉቀንና አቶ ሌሊሳ የተባሉት ሌሎች ወገኖች  እስረኞቹን ሊረዷቸው እንደሚፈልጉ እንደገለጹላቸውም ታውቋል። “እያሳዘንን ያለን ነገር ይህ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ባለበት አገር የሚጠይቀን ሰው ማጣታችን ነው” ሲሉ ምሬታቸውን በእንባ ገልጸዋል።

በወህኒ ቤቱ የሚገኙት ሃላፊዎችም ከህወሃት/ኢህአዴግ ጋር አብረው እየሰሩ እንደሚገኙ በሚመስልበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ ጥሰት እንኳን ለመስማት ፈቃደኛ አለመሆናቸው ተነግሯል። ከኢትዮጵያ ኢምባሲ ጋር እናገናኛችሁ እያሉ እንደሚጠይቋቸውና፣ እስረኞቹ ግን ጥያቄያቸውን ሳይቀበበሉ እንደቀሩ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።

በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ በግዳጅ እንዲመለሱ ከተደረጉት 9 ኢትዮጵያውያን ውስጥ 5ቱ ኢትዮጵያውያን አይደሉም በማለት የኢህአዴግ መንግስት ወደ አሜሪካ መመለሱ ይታወቃል።