መጋቢት 13: 2009)
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት በአሜሪካ በተዘጋጀ የአፍሪካ የንግድ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ የተጋበዙ እንግዶች የአሜሪካ የመግቢያ ቪዛ መከልከላቸውን የጉባዔው አዘጋጆች አስታወቁ።
በካሊፎርኒያ ግዛት በሚገኘ የደቡብ ካለፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የተዘጋጀው የንግድ ጉባዔ በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ለመምከር ቢዘጋጅም አንድም የአፍሪካ ተወካይ በቪዛ ችግር ሊገኝ አለመቻሉን ዘጋርዲያን ጋዜጣ አዘጋጆቹን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
ለሶስት ቀናት የተዘጋጀው የንግድ ጉባዔ የአፍሪካና የአሜሪካንን የቢዝነስ ትስስር ለማጠናከር ያለመ እንደነበር ሜሪ ፍላወርስ (Mary Flowers) የተሰኘ የጉባዔው አዘጋጅ ድርጅት ገልጿል።
ከኢትዮጵያ፣ ሴራሊዮን፣ ጊኒ፣ ጋና፣ ናይጀሪያ፣ አንጎላ፣ ካሜሩን፣ ደቡብ አፍርካና ሌሎች ሃገራት የተወከሉ እንግዶች የቪዛ ጥያቄያቸው ተቀባይነት ማጣቱ ታውቋል። በአጠቃላይ ከ60 እስከ 100 የሚደርሱ ተወካዮችና ጥናት አቅራቢዎች በአፍርካ ጉዳይ ላይ በተዘጋጀው የንግድ ጉባዔ ተሳታፊ ሳይሆኑ መቅረታቸውን አዘጋጆች ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
የቪዛ ጥያቄው ውድቅ መደረግ ከፕሬዚደንት ትራምፕ አልያም በየሃገሪቱ ካሉ ኤምባሲዎች የግል ውሳኔ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ የተረዳነው ነገር የለም ሲል ሜሪ ፍላወርስ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በአፍሪካና በአሜሪካ የንግድ ኩባንያዎች መካከል ሊካሄድ የተዘጋጀው ጉባዔ ለበርካታ ሰዎች ስራን የመፍጠር ዕድል ያለመ እንደነበር አዘጋጁ ተቋም አክሎ ገልጿል። በጉዳዩ ዙሪያ የተጠየቀው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በቪዛ መከልከሉ ዙሪያ ምላሽ ለመስጠት እንደማይፈልግ ማሳወቁን ዘጋርዲያን ጋዜጣ በዘገባው አስፍሯል።
የጉባዔው አዘጋጆች ተሳታፊ እንግዶች የቪዛ ክፍያን ከመፈጸም ባለፈ የተለያዩ የንብረት ባለቤትነት የሚያሳይ ማስረጃን አቅርበው እንደነበርና መቶ በመቶ የአፍሪካ ተሳታፊ ቪዛ ሲከለከል ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን አስታውቀዋል።
የአሜሪካ መንግስት ከአፍሪካ ጋር የቪዝነስ ትስስር መፍጠር ጠቃሚ እንደሆነ እየገለጸ በሩን መዝጋቱ ተገቢ አይደለም ሲል የጉባዔው አዘጋጆች አክሎ አመልክቷል።
ከአፍሪካ የተወከሉ ተሳታፊዎች የአሜሪካ የመግቢያ ቢዛ መከልከላቸውን ተከትሎ የንግድ ጉባዔው አዘጋጅ ሜሪ ፍላወርስ ተቋም የካሊፎርኒያ ግዛት ተወካይ ከሆኑት የምክር ቤት አባላት ጋር ምክክር መጀመሩን አክሎ ገልጿል።