በአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት የአፍሪካ ተጠሪ የሆኑት ጆኒ ካርሰን፣ ኢትዮጵያ ሶማሊያን ዳግም መውረሯ ትክክል አይደለም አሉ

ህዳር 13 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-ባለስልጣኑ ይህን ቃል የሰጡት ማክላቺ ለተባለው ጋዜጣ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከአራት አመት በፊት ሶማሊያን በመውረር ለሁለት አመታት ያክል በአገሪቱ ውስጥ ብትቆይም፣ በመጨረሻ አልሸባብን  መፍጠር በስተቀር ያመጣቸው ውጤት እንደሌለ ካርሰን ተናግረዋል።

ካርሰን በሶማሊያ ሰላም ለማምጣት ማንኛውም እንቅስቃሴ በአፍሪካ ሰላም አስከባሪ በኩል መካሄድ እንዳለበት በመግለጥ የኢትዮጵያን እንቅስቃሴ በእጅጉ ነቅፈዋል።

የመለስ መንግስት በድጋሜ ሶማሊያን ለመውረር ለምን እንደፈለገ ግልጽ ባይሆንም፣ የፖለቲካ ተንታኞች ሁለት ምክንያቶችን ያስቀምጣሉ። አንዳንድ ወገኖች የመለስ መንግስት በምርጫ 97 ማግስት ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ መግባቱን ተከትሎ፣ የህዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ለማስለወጥ ሲል ሶማሊያን መውረሩን በማስታወስ፣ አሁንም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዬው የህዝብ መከፋት እየጨመረ መምጣት ስጋት ላይ እየጣለው በመምጣቱ ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ መፈለጉን ያሳያል ይላሉ።

እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት መንግስት ራሱን በጦርነት ውስጥ እንደሆነ አድርጎ በማቅረብ በአገር ውስጥ የሚካሄደውን ተቃውሞ በጸረ ሽብር ትግል ስም ለመጨፍለቅ እንዲመቸው ለማድረግ የወሰደው እርምጃ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ የአካባቢው አገሮች በተለይም ዩጋንዳና ኬንያ በሶማሊያ ውስጥ ያላቸው ጉልበት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ፣ የመለስ መንግስት ከምእራቡ አለም የሚያገኘው የዲፕሎማሲና የገንዘብ ድጋፍ እንዳይቋረጥ በመስጋት የወሰደው እርምጃ ነው የሚሉ አሉ።

እንደ ማክላቹ ጋዜጣ ከሆነ ሶማሊያውያን የኢትዮጵያ ጦር ወደ አገራቸው መግባቱን አይደግፉም። የአልሸባብን አስተዳደር በርካታ ሶማሊያውያን እንደሚጠሉት ያስታወሰው ጋዜጣው ፣ አንዳንዶች የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያ ከሚገባ አልሸባብ ይግዛን እስከማለት መድረሳቸውን ገልጧል።

ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሶማሊያ መግባቱ እውነት ቢሆንም፣ መንግስት ግን አሁንም ጦሩ ወደ ሶማሊያ መግባቱን ያስተባብላል።