(ኢሳት ዜና–መስከረም 22/2010)በአሜሪካ ላስቬጋስ አንድ የ64 አመት ግለሰብ የሙዚቃ ትዕይንት ይከታተሉ በነበሩ ሰዎች ላይ በከፈተው የተኩስ ሩምታ 58 ያህል ሰዎች መግደሉ ተሰማ።
ግለሰቡ ካረፈበት ሆቴል 32ኛ ፎቅ ላይ በመሆን ለሙዚቃ በታደሙ ሰዎች ላይ በከፈተው ሩምታ ከ5 መቶ በላይ ሰዎች ቆስለው ሆስፒታል ገብተዋል።
ጅምላ ግድያው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1949 ወዲህ በአሜሪካ ታሪክ ከተፈጸሙ ወንጀሎች ዘግናኙ ተብሏል።
ያለምንም ርህራሄ ማንዴላይ ከተባለው ሆቴል 32ኛ ፎቅ ላይ ሆኖ የተኩስ እሩምታውን የከፈተው አሜሪካዊ ስቴፈን ፓዶክ ይባላል።
10 ያህል አውቶማቲክ ጠመንጃዎችን ይዞ በሆቴሉ የመሸገው የ64 አመቱ ሽማግሌ ስቴፈን ፓዶክ በሜዳማ ቦታ ላይ በክፍት መድረክ የሙዚቃ ትርኢት በመከታተል ላይ የነበሩ ከ22 ሺ በላይ በሚሆኑ ተመልካቾች ላይ የጥይት ናዳ እያከታተለ አርከፍክፎባቸዋል።
በተኩስ እሩምታው የተደናገጡት የሙዚቃ ታዳሚዎች ግማሾቹ እግሬ አውጪኝ ብለው በየጥጋጥጉ ሲተራመሱ ገሚሶቹ ደግሞ ባሉበት በሚርከፈከፍባቸው ጥይት እየጮሁ ሲወድቁ ታይተዋል።
በጥቃቱ እስካሁን 58 ያህል ሰዎች መሞታቸው ሲረጋገጥ በአደጋው ቆስለው ሆስፒታል የተወሰዱት ቁጥር ደግሞ ከ5 መቶ በላይ መድረሱ ታውቋል።
የተኩስ እሩምታውን በመክፈት ሰላማዊ ሰዎችን በጅምላ የረፈረፈው ስቴፈን ፓዶክ የልቡን ከሰራ በኋላ እራሱን ገድሎ ተገኝቷል።
በክፉ ልቦና ተነሳስቶ ይህን ዘግናኝ ጥፋት የፈጸመው ግለሰብ ወንጀሉን ለምን እንደፈጸመ ከወዲሁ የታወቀ ነገር አለመኖሩን ፖሊስ አስታውቋል።
የአካባቢው ፖሊስ አዛዥ ላምባርዶ ጅምላ ጭፍጨፋውን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ሰውየው ሜስኳይት ከተባለች የሰሜን ምስራቅ ላስቬጋስ አካባቢ የመጣ መሆኑ ከመታወቁ በስተቀር ስለ ግድያው ምክንያት እስካሁን ፍንጭ አልተገኘም።
የጅምላ ጥቃቱን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተኩስ እሩምታው ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች ጥልቅ ሀዘናቸውን አሰምተዋል።
ክስተቱንም እጅግ ፈታኝ ሁኔታና ሰይጣናዊ ድርጊት ሲሉም ገልጸውታል።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ክስተቱን በዘግናኝነት ቢገልጹትም ጉዳዩ ከሽብር ጋር የተያያዘ አይደለም ባይ ናቸው።
የአሜሪካ ፖሊሶች ከጅምላ ገዳዩ ስቴፈን ፓዶክ ጋር ነበረች የተባለች ሴትን እያፈላለጉ መሆናቸውንና ሴትዬዋ ከአሜሪካ ወጣ ባለ ስፍራ እንዳለች ማረጋገጣቸውን አስታውቀዋል።