(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 25/2011) በአማራ ክልል ጃዊ ወረዳ የተከሰተው የጸጥታ ችግር በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ።
በንጹሃን ላይ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የአማራና የቤንሻጉል ጉምዝ ክልሎች አስታውቀዋል።
የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ለኢሳት እንደገለጹት በጃዊ ወረዳ ሶስት ቀበሌዎች በተፈጸመ ጥቃት የተገደሉ ሰላማዊ ዜጎች ቁጥርና የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳት ለማወቅ ምርመራ በመካሄድ ላይ ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በጃዊ የተፈጸመውን የሰላማዊ ሰዎች ግድያን በማውገዝ ጥፋትን በጥፋት መመለስ ከባድ ዋጋ ያስከፍላል ብለዋል።
የአማራ ክልል በተሳሳተ ምስልና መረጃ ችግሩን የሚያባብስ አንድ ሚዲያ እንዳለም ገልጿል።
በአሁኑ ሰዓት መከላከያ ሰራዊት አካባቢውን በመቆጣጠር በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ማስቆሙንም ለመረዳት ተችሏል
ጃዊ ወረዳ አማራ ክልልን ከቤንሻንጉል ጉምዝ የምታዋስን በአማራ ክልል ስር የምትገኝ ወረዳ ናት።
የጉምዝና ሺናሻ ማህበረሰቦች በብዛት የሚኖሩባት ወረዳ እንደሆነች ይነገራል።
ሰሞኑን በአቅራቢያ በሚገኘውና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ውስጥ ባለው መተከል ዞን የተፈጠረው ችግር ለጃዊ ወረዳ የጉምዝና ሺናሻ ማህብረሰቦች አደጋን ይዞ መቷል።
ማንነታቸው ያልታወቁ በሚል የተገለጹና መሳሪያ የታጠቁ ሃይሎች በጃዊ ወረዳ ገብተው ሰላማዊ ነዋሪዎችን መግደላቸውን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።
ከባለፈው ሳምንት መጨረሻ አንስቶ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ለሁለት ቀናት በጃዊ ወረዳ በርካታ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን የአማራና የቤንሻንጉል ጉምዝ አመራሮች ገልጸዋል።
የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አበራ ባየታ ለኢሳት እንደገለጹት በጃዊ ወረዳ ሶስት ቀበሌዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።
ታጣቂዎቹ ከትላንት በስቲያ በወረዳዋ በመግባት ያገኙት ሰው ላይ ይተኩሱ ነበር ያሉት አቶ አበራ የተገደሉትን ቁጥር በተመለከተ ትክክለኛውን አሀዝ አሁን ላይ ለመግለጽ እንደማይቻል አስረድተዋል።
በአከባቢው በሚገኙ የተለያዩ የጤና ማዕከላት የገቡ ቁስለኞች ብዛትና ሁኔታ የሚያሳየው ጥቃቱ የከፋ እንደሆነ ነው ብለዋል ሃላፊው።
አጠቃላይ የተገደሉትንና የደረሰውን ጉዳት ለማወቅ ምርመራ በመደረግ ላይ መሆኑንም የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ባለስልጣናት ገልጸዋል።
ኢሳት በደረሰው መረጃ ላይ የጃዊውን ጥቃት ለማስቆም መከላከያ ሰራዊት በፍጥነት በመግባት አካባቢውን መቆጣጠሩንና ሊደረስ የነበረውን የከፋ ጉዳት ማስቀረት መቻሉን የሚያመለክት ነው።
የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ባለስልጣናትም የመከላከያ በቶሎ መድረስ አደጋውን በቶሎ ለመቆጣጠር እንዲቻል ማድረጉን ገልጸዋል።
የአዴፓ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ መንግስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት በሰጡት ቃለመጠይቅ ጥፋትን በጥፋት መመለስ የሚያስከፍለው ዋጋ ከባድ ነው በማለት የጃዊውን ጥቃት አውግዘዋል።
በዘር ማንነቱ የሰው ልጅ መገደሉ እጅግ የሚያሳዝን ነገር ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጃዊው ጥቃት ጥቁር ነጥብ ትቶ ያለፈ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ አሰማህኝ አስረስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በቤንሻንጉል ጉምዝ የተፈጸመውን ድርጊት ተከትሎ በድርጊቱ የተቆጡ አልያም በሌላ ምክንያት ማንነታቸው ባልታወቁ የታጠቁ ሃይሎች በጃዊ ወረዳ ግጭት አስነስተው የበርካታ ሰዎች ህይወት እንዲጠፋ አድርገዋል ብለዋል።
የክልሉ መንግስት በጃዊው ጥቃት ዙሪያ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ወደ ስፍራው አንድ ቡድን ልኮ በማጣራት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።
ድርጊቱ ግን ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል አቶ አሰማህኝ።
የአንድ ግለሰብ ወይም ፓርቲ ልሳን የሆኑ የሚዲያ ኔትወርኮች በሀሰተኛ ምስልና መረጃ ችግሩን እያባባሱት ነው ሲሉም አቶ አሰማህኝ አስረስ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ጠቅሰዋል።
የትኛው ሚዲያ እንደሆነ ግን በስም ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
በአሁኑ ሰዓት መከላከያ ሰራዊት በዋናነት በአካባቢው ተሰማርቶ የሰላም ማስከበር ስራውን እያከናወነ ሲሆን የሁለቱ ክልሎች የጸጥታ ሃይሎችም በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።