(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 27/2010)በአማራ ክልል የጦር መሳሪያ ለማስፈታት የተደረገው ዘመቻ ውጤታማ አለመሆኑን ተከትሎ ለሚሊሺያ ሰራዊት አባላት ጥሪ መደረጉ ተሰማ።
ወደየቤተሰቦቻቸው የተበተኑት የሚሊሺያ አባላቱ በኮማንድ ፖስቱ ስልጠና ከወሰዱ በኋላ መሳሪያ ወደ ማስፈታት ዘመቻ እንዲገቡ መታቀዱን የኢሳት ምንጮች ካደረሱን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
የህወሀት አገዛዝ የአማራ ተወላጆችን በጦር መሳሪያ ማስፈታት ዘመቻ እርስ በእርስ ለማጋጨት ያቀደው ሴራ በመሆኑ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ ጥሪ ቀርቧል።
የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ አገዛዝ በተለይም በአማራ ክልል የጦር መሳሪያ ለማስፈታት የከፈተው ዘመቻ ከፍተኛ ኪሳራ እንደገጠመው መረጃዎች ያሳያሉ።
በጎጃም፣ በሰሜንና ደቡብ ጎንደር በተለያዩ አካባቢዎች የተካሄደው ዘመቻ ከህዝቡ በገጠውም ርምጃ በትንሹ ከ10 ያላነሰ የኮማንድ ፖስት ወታደሮች የተገደሉ መሆኑ የሚታወስ ነው።
በሰሜን ጎንደር አርማጭህ ሮቢት ላይ የገጠመው ብርቱ ውጊያም በመሳሪያ ማስፈታት ዘመቻ ከደረሱበት ሽንፈቶች የሚጠቀስ ነው።
አገዛዙ የመሳሪያ ማስፈታቱን ዘመቻ ለማሳካት በሌላ አቅጣጫ መምጣቱን የሚያሳይ መረጃ ነው ለኢሳት የደረሰው።
በአማራ ክልል የሚገኙ የሚሊሺያ ጦር አባላትን ወደ መደበኛ ህይወት ከገቡበት እንዲመለሱና ስልጠና ወስደው የጦር መሳሪያ የማስፈታት ዘመቻውን እንዲያደርጉ መታቀዱን የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።
ለዚህም ለሚሊሺያ አባላቱ ጥሪ ተደርጎ ወደስልጠና መግባታቸው ታውቋል።
ከነባር የሚሊሺያ አባላት በተጨማሪ በአርሶአደሩ ውስጥ የሚገኙ ታጣቂዎችንም በሚሊሻነት እና በተጠባባቂ ሃይል ውስጥ እንዲገቡ ለማድረግ በሚል በተለያዩ ወረዳዎች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑም ተገልጿል።
ስልጠናው በተቃውሞ የታጀበ መሆኑም ነው የተገለጸው።
በየወረዳዎች የሚሊሻ ሀላፊዎችና አባላት ስለኮማንድ ፖስቱ ስልጠና በሚሰጥበት ጊዜ መሳሪያ መግፈፍ ለምን አስፈለገ የሚል ጥያቄ በከፍተኛ ሁኔታ አጨቃጫቂ ሆኗል።
በሚሊሻ አመራሮቹ የተመለመሉ አርሶአደሮች በወረዳ ከተሞች የቀን የውሎ አበል 35 ብር እየታሰበላቸው በማዘጋጃ አዳራሾች እንዲያድሩ እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት የተወሰኑት ገንዘቡ ለምግብ እንኳን የሚበቃ አይደለም በማለት ወደየመጡበት ጥለው መሄዳቸው ታውቋል።
በዚህ ሳምንት የኮማንድ ፖስት ሃላፊዎች እንደአዲስ በገንዘብ በመደለል ጠቀም ያለ አበል እንከፍላለን በሚል ለ3 ቀናት ስለኮማንድ ፖስቱ ስልጠና መሰጠቱም ታውቋል።
በምዕራብ ጎጀም ሜጫ ወረዳ መርዓዊ ከተማ ፣ በሰሜን ጎንደር ቋራ ወረዳ ገለጎ ከተማ በደቡብ ጎንደር ላይ ጋይንት ወረዳ ንፍስ መውጫ ከተማ ፣ በአዊ ዞን ጓንጓ ወረዳ ቻግኒ ከተማ ስልጠናው ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች የሚጠቀሱ ናቸው።
በየስልጠናው ላይ በሌሎች ክልል ህዝቡ እንዲታጠቅ እየተደረገ ለምን በአማራ ክልል መሳሪያ ለመግፈፍ ታሰብ ፣ ለምን መሳሪያ ይነጠቃል ? በሚል ከፍተኛ ውዝግብ ተነስቶ እንደነበርም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የኮማንድ ፖስቱ አመራሮች ያለ ክልሉ መንግስት እውቅና በሚያደርጉት በዚህ ስልጠናና ስብሰባ ለተነሱት ጥያቄወች ሲመልሱ ስርዓቱን የሚቃወሙትን ብቻ ነው መሳሪያ የምንነጥቀው በማለት መናገራቸውም ታውቋል።
ከዚህ በፊት በአማራ ክልል በተደጋጋሚ ተሞክሮ ያልተሳካው የህዝቡን የመሳሪያ ገፈፉ ዛሬም መልኩን ቀይሮ በገዛ ወገኖቹ ለማካሄድ እየተሞከረ ይገኛል።
ይህ አካሄድ በአማራ ተወላጆች መሃል የእርስ በእርስ ግጭት በመፍጠር ላይ ያለመ በመሆኑ ህዝቡ ነቅቶ እንዲጠብቅ በስልጠናው ላይ የሚገኙ ሚሊሻዎችና ምልምል አርሶአደሮች ጥሪ ማቅረባቸው የኢሳት ወኪል ከላከልን ዜና ለማወቅ ተችሏል።