ጥር ፴ (ሠላሳ)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአማራ ክልል የሚታየውን የጸጥታ ሁኔታ ለመገምገም ከፌደራል የተላከው የኮማንድ ፖስቱ አጣሪ ቡድን ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቢነሳ ህዝቡ በቀጥታ በመንግስት ላይ ከእስካሁኑ የከፋ ጥቃት ሊሰነዝር ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።
ኮማንድ ፖስቱ “ የክልሉን ህዝብ ገትቶ የያዘው መሳሪያ ነው” ያለ ሲሆን፣ አዋጁ ቢነሳ ከእስካሁኑ በከፋ ሁኔታ አመፁን ለማስቀጠል ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠናል” ብሎአል፡፡
ለአንድ ወር ያክል በጎንደር፣ በባህርዳር እና በአዊ ዞን የተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውሮ የህዝቡን ሁኔታ ማጥናቱን የሚገልጸው የፌደራል ኮማንድ ፖስት ቡድን፣ በአማራ ክልል የተካሄደው ተሃድሶ የይምሰል እና ስር ያልስደደ ነው ሲል አጣጥሎታል። ተሃድሶው “ትዕዛዝ ለመፈፀም የሚደረግ ከመሆኑም በላይ መንግስትንና ህዝብን ከማቀራረብ ይልቅ ከታለመው ዓላማ ውጭ በመውጣት መንግስትና ህዝብን የሚያቃቅር ፣ ለስርዓቱ የማይጠቅም እንዲሁም በስህተቶች የታመቀ ሆኖ ተጠናቋል ብሎአል።
ሰኞ እለት ለኮማንድ ፖስቱ ወታደራዊ ክፍል የቀረበው ሪፖርት እንደሚያትተው፣ በአማራ ክልል የጥልቅ ተሃድሶው መንገድ መስሩን መሳት ብቻ ሳይሆን፣ በመንግስት እና በህዝቦች መካከል ቅራኔ መፍጠርን ቀዳሚ ያደረገ ነው ይላል።ተሃድሶው “በህዝቦችና በመንግስት መካከል መቃቃርን አስፍቶ፣ በጎንደር እና በክልሉ የተደረጉት ህዝባዊ አመጾች ትክክለኛ መሆናቸውን መንግስት ጥፋቱን እንዳመነ አድርጎ በማቅረብ እንዲሁም መንግስት ባደረገው የስልጣን ሽግሽግም ለለውጥ መዘጋጅቱን ሳይሆን የ ስራ ዝውውር እንዳወጣ ተደርጎ እንዲታይ አድርጓል በማለት ይተቻል። ”
የኮማንድ ፖስቱ አጣሪ ቡድን “ህዝቡ ከአመፅ የተገታው በአስቸኳይ አዋጁ በተሰጠው መመሪያ እና ትእዛዝ እንጅ በፍላጎቱ ባለመሆኑ ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፍኖ ባይዘው ኖሮ አመፁ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ለማረጋገጥ ችለናል” ብሎአል፡፡ የኮማንድ ፖስቱ አጣሪ ቡድን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማሻሻልም ሆነ ማንሳቱ እንደማይመክር ያሳስባል፡፡
አጣሪ ቡድኑ በሪፖርቱ “ በክልሉ በህቡዕ የተደራጁ ሐይሎች መኖራቸውን አረጋግጠናል” ያለ ሲሆን፣ “ተደጋጋሚ የቦንብ ጥቃቶች መኖራቸው እና አሁንም ህዝቡ ለመንግስት እየሰጠ ያለው ምላሽ እና በተለያዩ በሄድንባቸው ከፍተኛ የክልሉ ተቋማት ከህዝቡ ያገኘነው ምላሽ ጥላቻን ያዘለ በመሆኑ የአስቸኳይ አዋጁ ጊዜ መራዘም እንደሚኖርበት” አፅንኦት እንሰጣለን ብሎአል።
የኮምንድ ፖስቱ አጣሪ ቡድን፣ ጥልቅ ትሃድሶው በጥራት እየተካሄደ ባለመሆኑ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ለምዕራብ እዝ ጦር በአድራሻ እና ለአማራ ክልል መንግስት እና ለብአዴን በግልባጭ ደብዳቤ ጽፏል። ይሁን እንጅ የማስተካከያ እርምጃው በምን መልኩ እንደሚወስድ ዝርዝር ነገር ባለመጻፉ የብአዴን ባለስልጣናት ግራ መጋባታቸው ታውቋል።