(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 14/2010)
በአማራ ክልል የተጠራው የስራ ማቆምና በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ዛሬም መካሄዱ ተገለጸ።
በተለይ በጎንደር አድማው ቀጥሎ የዋለ ሲሆን በባህርዳርም በአብዛኛው የከተማው ክፍል ሱቆችና መደብሮች ተዘግተው መዋላቸው ታውቋል።
አስቸኳይ አዋጁን በመጣስ የተጠራውና ለሶስት ቀናት እየተካሄደ ያለው በቤት ውስጥ የመቀመጥና የስራ ማቆም አድማ በተለይ በጎንደርና በባህርዳር በስፋት ተካሄዶ በተቀመጠው ግዜ ሰሌዳ ዛሬ ማምሻውን ተጠናቋል።
በጎንደር እንደባለፉት ሁለት ቀናት ሱቆች መደብሮች፣ አገልግሎት መስጪያ ተቋማት ተዘግተዋ የዋሉ ሲሆን የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ እንዳልነበረ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የከተማው የመንግስት ባለስልጣናት አድማውን በመቱ ተሽከርካሪዎች ላይ የ5ሺህ ብር ቅጣት እንደሚጥል በመግለጽ ቢያስጠነቅቅም ለወደቀ መንግስት አንታዘዝም በማለት ህዝቡ በአቋሙ ጸንቶ አድማውን መቀጠሉን ነው ለማወቅ የተቻለው።
የአድማውን ጥሪ ወደጎን በመተው ሲንቀሳቀስ በነበረ አንድ ተሽከርካሪ ላይ ጥቃት ተፈጽሟል።
በጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በሞጣ፣ በቢቸና፣ በደብረ ታቦር፣ በፍኖተ ሰላም፣ በቻግኒና በሌሎች ከተሞች የንግድ ተቋማት ተዘግተው እንደነበርም የአገዛዙ ደጋፊ የሆነው ሪፖርተር ጋዜጣም ዘግቧል።
የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባበል አድማው መደረጉን ገልጸው እያስከፈትን ነው ማለታቸውን ሪፖርተር ጠቅሷል።
በባህርዳርም አድማው ለሶስተኛ ቀን ሲካሄድ የዋለ ሲሆን አብዛኞቹ ሱቆችና መደብሮች አድማውን ተሳትፈዋል።
በተለይም ቀበሌ 11 አባይ ማዶ፣ በግ ተራ፣ ቀበሌ 4 እና 14 የሚገኙ የንግድ ቦታዎች ተዘግተው እንደነበር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የባህርዳር ከተማ ባለስልጣናት አድማ የመቱ የንግድ ቦታዎችን በማሸግ ስራ ላይ ተጠምደው መዋላቸው ታውቋል።
ትራፊክ ፖሊሶችም በአድማው የተሳተፉ ተሽከርካሪዎችን ሰሌዳ ሲፈቱ ውለዋል።
በሌላ በኩል በሰሜን ወሎ መርሳ አካባቢ የሚገኘው ድልድይ ትላንት መሰበሩ ታወቀ።
ድልድዩ የተሰበረው ባልታወቁ ሃይሎች በተፈጸመ ጥቃት ነው የሚል መረጃ ቢወጣም አገዛዙ ከባድ ዝናብ በመጣሉ አደጋው እንደደረሰ አስታውቋል።
በድልድዩ ላይ በደረሰው አደጋም ከአዲስ አበባና ደሴ ወደ ወልዲያና ሰሜን አቅጣጫ የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ መቋረጡ ታውቋል።
የአገዛዙ ባለስልጣናት ተለዋጭ መንገድ እስኪሰራ ህዝቡ በትዕግስት እንዲጠብቅ ጠይቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በሰሜን ወሎ ዞን ዋጃ ጥሙጋ አካባቢ የህዝብ ተቃውሞ መከሰቱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ትላንት ማታ በጀመረው በዚሁ ተቃውሞ በመንግስት ተቋማት ላይ ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን የአንዳንድ መስሪያ ቤቶች ህንጻ መስታወታቸው መሰባበሩን ለማወቅ ተችሏል።
ዘግይቶ በደረሰን ዜናም ባህርዳር በሚገኘው የመከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅት መኮድ ግቢ የእሳት ቃጠሎ መድረሱ ተሰማ።
ቃጠሎው በጥቃት ይሁን በሌላ ምክንያት የታወቀ ነገር የለም።
እስከ ቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በቆየው በዚሁ ቃጠሎ በግቢው ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ንብረቶች መውደማቸውን የደረሰን ዜና አመልክቷል።