በአማራ ክልል የተከሰተው ህዝባዊ ተቃውሞ ጸረሰላም ሃይሎች የፈጠሩት ነው ሲል የአማራ ክልል ምክር ቤት ገለጸ

ኢሳት (ኅዳር 14 ፥ 2008)

የአማራ ክልል ምክር ቤት በክልሉ የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ የመልካም አስተዳደር ችግርና ጸረ-ሰላም ሃይሎች የፈጠሩት ችግር ነው በሚል ከተወያየ በኋላ የካቢኔ ሹም ሽር በማድረግ ተጠናቀቀ።

በአቶ አንዳርጋቸው ገዱ ቀርበው በምክር ቤቱ ከጸደቁት 22 የቢሮ ሃላፊዎች 10ሩ ነባር ሃላፊዎች ሲሆኑ፣ 12 ደግሞ አዳዲሶች ናቸው። gedu-andargachew

ከ12ቱ አዳዲስ የቢሮ ሃላፊዎች 6ቱ በአማራ ክልል ዩኒቨስቲዎች ሲያስተምሩ የነበሩ ሲሆኑ፣ የብዓዴን አባላት በመሆን በብዓዴን/ኢህአዴግ ዕገዛ ትምህርታቸውን እስከ ፒኤች ዲ ድረስ የተማሩ መሆናቸውን ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።

በአማራ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ እምቢተኝነት ተከትሎ በፓርቲውና በክልሉ አመራር ላይ የሰላ ትችት ሲያቀርቡ የነበሩት የገንዘብና ኢኮኖሚ ቢሮ ሃላፊ አቶ አየነው በላይ ግምገማውን ተከትሎ ከስልጣናቸው ተነስተዋል።

በአንጻሩ የህዝቡን ተቃውሞ ለማፈን በተካሄደው ግድያና እስር እጃቸው አለበት የሚባሉት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ብናልፍ አንዷለም ባሉበት እንዲቀጥሉ ተደርጓል።

አቶ ገዱ በአማራ ክልል ጥቃት ደርሶባቸዋል የተባሉ የትግራይ ተወላጆችን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ በህወሃት አገዛዝ ጫና እንደተደረገባቸው ይነገራል።

ይሕንኑ ተከትሎም የወልቃይት የማንነት ጥያቄ በትግራይ ክልል የሚፈታ ነው ተብሎ ታልፏል።