ኅዳር ፳፫ (ሃያ ሦስት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአማራ ክልል ውስጥ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ውስጥ ለሚሰሩ የብአዴን አባላት በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጥልቅ ተሃድሶ በሚል ግምገማ ተጀምሯል። በክልሉ የውሃ ሃብት ውስጥ የሚሰሩ የብአዴን አባላት በአማራ ክልል መሰብሰቢያ አዳራሽ ዓርብ ሕዳር 23 ቀን 2009 ዓ.ም የተጀመረው ስብሰባ ከተወያዮቹ ከፍተኛ ተቃውሞዎች ቀርበውበታል።
ስብሰባውን በዋና አወያይነት የመሩት በአማራ ክልል የምእራብ አማራ የውሃ ስራዎች ድርጅት ምክትል ስራ አስኪያጅ እና የቀድሞው አዊ ዞን አስተዳዳሪ ነበሩት አቶ ፈለቀ አቡኔ ነበሩ። ሕዝባዊ እምቢተኝነት ተከትሎ መብታቸውን የጠየቁ ዜጎችን በተለይ በወጣቶች ላይ ያነጣረውን የጅምላ ጭፍጨፋ እና እስራት በዋናነት ሲያስፈጽሙ የነበሩት አቶ ፈለቀ አቡኔን ተሰብሳቢዎቹ በጥያቄ አፋጠዋቸዋል። ከመስሪ ቤቱ የብአዴን አባላት ሰራተኞች ይዛችሁት የቀረባችሁት ጥልቅ ተሃድሶ የሚለው ማወያያ እራሱ ምንም አዲስ ነገር የለውም፣ እስካሁን ድረስ እንዳየነው በአገር አቀፍ ደረጃ ላሉት ችግሮች ምንም ዓይነት ሁነኛ የሆነ ዘላቂ መፍትሔዎች አልተሰጡም።
የቀረበው ሪፖርት እራሱ መልስ ሰጪ እና ችግር ፈቺ አይደለም። ተሃድሶው እናንተ እንደምትሉት ሁሉን ያካተተ ጥልቅ ተሃድሶ አይደም። የሚሉ የተለያዩ ሞጋች ጥያቄዎች እና ተቃውሞዎችን በማንሳት ተሰብሳቢዎቹ የቀረበውን ሪፖርት ውድቅ አድርገውታል። ውይይቱ ለሁለተኛ ቀን በነገው እለትም ቀጥሎ የሚውል ሲሆን የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና ምክትል ፕሬዚዳንቱ ዓለምነው መኮንን ጨምሮ በስብሰባው ላይ ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮቻችን አክለው ገልጸዋል።