ነሃሴ ፲፰ ( አሥራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአንዳንድ አካባቢዎች አስተዳዳሪዎች ለቀው በመውጣታቸው ህዝቡ ራሱን እየመራ ነው። የመከላከያ ሰራዊት አፋጣኝ መልስ ካልተሰጠ ከተሞችን ጥለን እንወጣለን እያሉ ነው።
በባህርዳር የተጀመረው የስራ ማቆምና ከቤት ያለመውጣት አድማ ለአራተኛ ቀን እንደቀጠለ ባለበት በዚህ ወቅት ጎንደር ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ አድማውን የጀመረ ሲሆን፣ በምዕራብ ጎጃሟ ፍኖተሰላም ከተማ ደግሞ ከስራ ማቆም አድማው በተጨማሪ ህዝቡ ወደ አደባባይ በመውጣት እና ድምጹን በማሰማት ተቃውሞውን ሲያሰማ ውሎአል። ሰልፉን ለመበትን ጥይቶች ቢተኮሱም ህዝቡ ወደ ፊት በመግፋት ተቃውሞውን የብአዴን/ ኢህአዴግ አርማዎችን በማውደም፣ ከእንግዲህ በኢህአዴግ አንገዛም ሲል አቋሙን አሳውቋል። የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ፣ በኦሮሞ ወገኖች ላይ የሚፈጸው ግድያ ይቁም የሚሉና ለውጥን የሚጠይቁ መፈክሮች ተሰምተዋል። ወደ ባህርዳርና አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ በመዘጋቱ ከብር ሸለቆ የተነሳው መከላከያ ሰራዊት መግቢያ አላገኘም። ህዝቡ የኢህአዴግን ሰንደቃላማ በማውረድ አርማ የሌለው ሰንደቃላማ ሰቅሏል። ሰንደቃላማው እስከምሽት ድረስ ሳይወርድ ሲውለበለብ እንደነበር ነዋሪዎች ገልጸዋል። የክልሉ ም/ፐሬዚዳንት እና የትምህርት ክፍል ሃላፊው አቶ ብናልፍ አንዱአለም ቤትም ተደብድቧል።
የጎንደር ከተማ ህዝብ ደግሞ መጀመሪያ ላይ ካካሄደው የስራ ማቆም አድማ ልምድ በመውሰድ አድማውን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ሲሆን፣ ነጋዴዎች የንግድ ድርጅቶቻቸውን እንዲከፍቱ ቢገደዱም አሻፈረኝ ብለዋል። ፍጹም የመንፈስ አንድነት በተሞላበት ሁኔታ አድማው እየተካሄደ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በጎንደር ከተማ የተሰማሩ ወታደሮች፣ ለህዝቡ ጥያቄ አፋጣኝ መልስ ካልተሰጠ በዚህ ሁኔታ አንቀጥልም፣ እኛም ከህዝብ ጎን መቆማችን አይቀርም በማለት ማስጠንቀቂያ መስጠታቸው ታውቋል። የስራ ማቆም አድማውን እንዴት እንደሚቆጣጠሩት ግራ የገባቸው ወታደሮች፣ አንዳንድ ወገኖችን እየጠሩ በማበረታታት ላይ ናቸው።
በደባርቅ ከተማ የተጀመረው አድማም ለሁለተኛ ቀን ሲቀጥል፣ በቆላ ድባ እና አጎራባች ከተሞች ደግሞ አድማው ለሶስተኛ ቀን ቀጥሎአል። በደንቢያ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት በብአዴን ስም የሚንቀሳቀሱ የህወሃት አባል ናቸው የሚባሉት አቶ አብዱረህማን አህመድ አካባቢውን ጥለው ከጠፉ ጀምሮ የአካባቢው ህዝብ ራሱን ባረሱ በማስተዳደር ላይ ነው። ከአዘዞ እስከ ደንቢያ ባሉት ከተሞች የተጀመረውን አድማ አርሶአደሮችም የተቀላቀሉት በመሆኑ ግብይት ቆሟል።
የባህርዳር ከተማን የረቡዕ ወሎ በተመለከተ ዘጋቢያችን እንደገለጸው በገዢው ፓርቲ ታጣቂዎች በርካታ ጫና የደረሰባቸው የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች ጫናውን በመቋቋም የአራቱን ቀን ስራ ማቆም አድማ በድል አጠናቀዋል፡፡
በመጨረሻው ቀን በከተማዋ የሚንቀሰሳቀሱ በርካታ የታጠቁ ኃይሎች ሱቆችን ለማስከፈት ጥረት ቢያደርጉም፣ የባህር ዳር ህዝብ ግን ሁሉንም ተቋቁሞ የታሰበውን ማድረግ ችሏል፡፡
ጠዋት ተገደው የከፈቱ የተወሰኑ ሞባይል ቤቶችም ረፋዱ ላይ በመዝጋት አጋርነታቸውን አሳይተዋል፡፡ ባህር ዳር ህዝብ ከአሁን በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አንድነቱን ያሳየበት ይህ የስራ ማቆም አድማ፣ የከተማው ማህበረሰብ ለስርዓቱ ያለውን ጥላቻና በቃኝ ማለቱን ያስመሰከረበት እንደሆነ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
የአጋዚ ወታደሮች ያለምንም መሳሪያ በባዶ እጁ የወጣውን የባህር ዳር ነዋሪ ያለርህርሄ የገደሉበትን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የተከናነው ይህ ትግል ፣ አሁንም በተደራጀ መልኩ የህዝቡ ጥያቄ እስኪመለስ ሊቀጥል እንደሚገባ ነዋሪዎች አሳስበዋል፡፡
ተመሳሳይ የስራ ማቆም አድማ በዳባት እና ደጀን ከተሞች ነገ፣ በደብረታቦር ከተማ ደግሞ ከነሃሴ 22 ቀን 2008 ዓም ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።
በአብዛኛው የክልሉ ከተሞች የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን፣ የስልክ አገልግሎትም እየተቆራረጠ ነው። ህዝቡ የኢህአዴግ የንግድ ድርጅቶች በሆኑት ዳሸን ቢራና በመሳሰሉት ምርቶች ላይ የጣለው ማእቀብ ውጤት እያመጣ መሆኑም ታውቋል።
ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ተቃውሞውን ለመብረድ አንዳንድ አመረሮችን ገምግሞ ለማባረር ውሳኔ ያሳለፈ ቢሆንም፣ ህዝቡ ግን ገምጋሚዎችንም አስገምጋሚዎችንም ከእንግዲህ ማየት አንፈልግም እያለ ነው።