በአማራ ክልል የሚሰሩ ባንኮች ለክልሉ ተወላጆች ተፈላጊውን ብድር እንደማያመቻቹ ተነገረ፡፡

 

ሐምሌ  ፳፩ ( ሀያ አንድ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በክልሉ ውስጥ ለሚካሄዱ የኢንዱስትሪ ግንባታዎች ባንኮች ተገቢውን የብድር አገልግሎት እንዳይሰጡ በተዘዋዋሪ ስለሚከለከሉ ክልሉ እንደ አዋሳኝ ክልሎች የኢንዱስትሪ ዕድገቱ የተፋጠነ እንዳይሆን መደረጉ ቁጭት እየፈጠረባቸው መሆኑን ከፍተኛ የባንክ ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡

ከሁሉም ክልሎች ከፍተኛ የቁጠባ ገንዘብ የሚከማቸው በአማራ ክልል ውስጥ ቢሆንም ከተከማቸው ውስጥ በብድር የሚቀርበው ግን ሃያ በመቶ ብቻ መሆኑን የሚናገሩት ባለሙያው ብድሩን ለመፍቀድ የሚወስደው ጊዜ መርዘምም ከአጎራባች ክልል በእጅጉ የበዛ ተስፋ አስቆራጭ መሆኑ ሆን ተብሎ የክልሉን እድገት ለማደናቀፍ የሚሰራ ተንኮል እንደሆነ መረዳታቸውን ይገልጻሉ፡፡

ህብረተሰቡ ገንዘብ በዘመቻ እንዲቆጥብ የሚደረግበት አሰራር ቢኖርም የሚቆጠበውን ገንዘብ መልሶ ለክልሉ ልማት ለማዋል የሚያስችል አሰራር ባለመኖሩ የአማራ ክልል ባንኮች ገንዘቡን ወደ ሌላ ክልል እንዲሄድ በማድረግ ህጋዊ ዘረፋ በክልሉ ህብረተሰብ ላይ እያካሄዱ መሆኑን ባለሙያው  ገልጸዋል፡፡

በብሄራዊ ደረጃ የብድር አገልግሎት ሃላፊ ሆነው የሚሾሙ የክልሉ ተወላጆችም ብድር የሚፈቅዱት ለሌላ ክልል ተወላጆች እንጅ የገንዘቡ እንቅስቃሴ ወደክልሉ እንዳይገባ ተጽእኖ እንደሚደረግባቸው አብራርተው ተበዳሪዎችም ገንዘቡን ከአማራ ክልል ወስደው በሌላ ክልል የሚገነቡበት አሰራር መታየቱ ህጋዊ ዘረፋ በክልሉ ላይ እየተካሄደ መሆኑን እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡

ከፍተኛውን ውጣ ውረድ አልፈው የተበደሩት የክልሉ ተበዳሪዎች ሙሉ በሙሉ የተበደሩትን ያለምንም ችግር ሲመልሱ በአጎራባች ክልሎች የተበደሩ ደንበኞች ግን በአመላለስ ዙሪያ ችግር ፈጥረው ጉዳያቸው ጋዜጦችን እንደሚያጣብቡ ባለሙያው አክለዋል።