በአማራ ክልል ካሉ ትምህርት ቤቶች 87 ከመቶ የሚደርሱት ከደረጃ በታች ናቸው ተባለ

ሚያዝያ ፪ (ሁለት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በክልሉ ያለው የመማር ማስተማር ሂደት ከጊዜ ወደ ጊዜ ተቆርቋሪ እያጣ ነው ተብሎአል።
መሠረታዊ የግብዓት እጥረት መኖር ፣ የመምህራን ድጋፍ ማነስ፣ የወላጆች ክትትልና ድጋፍ አለመኖር፣የተማሪዎች የመማር ፍላጎትን ከመቀነስ አልፎ 87 በመቶ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች እንዲሆኑ ምክንያቶች መሆናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ መገምገሙን ገለጸ፡፡ ብዙዎቹ ተማሪዎች በአቅራቢያቸው ትምህርት ቤት የለም፡፡ በዚህ የተነሳ ተማሪዎች ተነሳሽነት ጎድሏቸው በትምህርታቸው ቸልተኛ እንዲሆኑ ማድረጉን የገለጹት የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙላው አበበ ከርቀት እየተንገላታ የሚማር ተማሪ በአቅራቢያው ትምህርት ቤት ካለው ተማሪ ጋር እኩል ውጤታማ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም በማለት ይገልጹታል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም ከዚህ ሁሉ ዋነኛ ችግር የግብዓት አለመሟላት እንደሆነ ተናግረው ግብዓት ተሟልቶላቸው በመስራት ላይ ያሉ 13 በመቶ ያክሉ ብቻ በመሆናቸው ትምህርት ቤቶች ትውልዱን በተገቢው መንገድ ሊቀርጹ እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡
የ10ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱት የክልሉ ተማሪዎች መካከል ወደ ቀጣዩ የክፍል ደረጃ ማለፍ የቻሉት በ2006 ዓ.ም ወደ 46 በመቶ፣ በ2007 ዓ.ም ደግሞ ወደ 45 በመቶ እና በ2008 የትምህርት ዘመን 32 ነጥብ 49 በመቶ መውረዱ የትምህርቱ ጥራት ከዕለት ወደ ዕለት እየወረደ መምጣቱ አስደንጋጭ መሆኑን ያልሸሸጉት ዳይሬክተሩ ይህ በክልሉ ያለው የመማር ማስተማር ሂደት ከጊዜ ጊዜ ተቆርቋሪ እያጣ መሆኑን ተናገረዋል፡፡
በተለይ ባለፈው ዓመት የተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት ከተማሪ እስከ ወላጅና አስተማሪ፣ ከትምህርት ቤት እስከ ትምህርት ቢሮ መሥራት የሚገባውን ባለመሰራቱ መሆኑን ባለስልጣኑ ገልጸው፣ መምህራንን በተነሳሽነት ማነስ ተጠያቂ አድርገዋል።
የ10ኛ ክፍል ውጤት ያልመጣላቸው ተማሪዎች ወደ መምህርነት ሙያ ስለሚገቡ የትምህርት ጥራቱ እየወረደ መጥቶ ያስከተለው ጉዳይ እንደሆነ በትምህርት ባለሙያዎች የሚነገረው አስተያየት ትክክል መሆኑን ያመኑት አቶ ሙላው የውጤቱ ማነስ ከመምህራን አቅም ማነስም የሚመነጩ ችግሮች እንዳሉበት አመላካች ነገሮች እንደታዩበት ተናግረዋል። ለትምህርት ጥራት መውደቅ መምህራን በበኩላቸው የኢህአዴግን መንግስት ግንባር ቀደም ተጠያቂ ያደርጋሉ።
የመምህራን የስራ ምዘና እና ሌሎችም የትምህርት እድሎች በቅድሚያ ለኢህአዴግ ፓርቲ ደጋፊዎች እንደሚሰጥ መምህራን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።