በአማራ ክልል ካሉት ትምህርት ቤቶች መስፈርቶችን የሚያሟሉት ከ 30 በመቶ አይበልጡም ተባለ።

መስከረም ፳፩ (ኅያ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ይህን ያሉት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የህዝብ ግንኙነት ዋና የስራ ሂደት መሪ አቶ ስዩም አድማሱ ናቸው።
ሀላፊው በ2002 ዓ.ም በታቀደው የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ በትምህርት ዘርፍ በርካታ ያልተሳኩ የአፈጻጸም ችግሮች መኖራቸውን ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ባለፉት አምስት ዓመታት በትምህርት ዘርፉ የታቀዱ ስራዎች የአፈጻጸም ችግሮች እንደታዩባቸው በዝርዝር አስረድተዋል።
ምክትል ቢሮ ኃላፊው የአዲሱን ዓመት የትምህርት አጀማመርና የሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መግቢያ አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በወሳኝነት ሊፈጸሙ እየተገባ ያልተሳኩ በማለት ከጠቀሷቸው ችግሮች መካከል አንዱ የትምህርት ቤቶች ደረጃ ችግር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለጥራት ወሳኝ መለኪያ የሆነው የትምህርት ቤቶች የውስጥ አደረጃጅት መሟላት መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው፤ በክልሉ የሚገኙ አብዛኛው ትምህርት ቤቶች የተሟላ የውስጥ አደረጃጀት እንደሌላቸው ገልጸዋል ፡፡
እንደ ሀላፊው ገለጻ በዓለምና በሃገር አቀፍ ደረጃ የወጡ የመመዘኛ መስፈርቶችን የሚያሟሉ ትምህርት ቤቶች በክልሉ ከ 30 በመቶ አይበልጡም።

በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ዙሪያም የተያዘው የአምስት ዓመት ዕቅድ በታላቅ ድክመት እንደተጠናቀቀ የክልሉ ኃላፊዎች ማመናቸውን በጋዜጣዊ መግለጫው የተናገሩት ምክትል የቢሮ ኃላፊው ፤ በየትኛውም የኢኮኖሚ ዘርፍ ታላላቅ ለውጥ የሚያመጡ ዕድገቶች የሚመዘገቡት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋን ቢሆንም፤ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ግን እቅዱን ማሳካት አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡
በ2002 ዓ.ም እንደ ክልል 60፤ በሃገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ 62 በመቶ የትምህርት ሽፋን ለማድረስ ቢታቀድም በክልሉ ያለው ሽፋን ግን ከግማሽ አንሶ 36 በመቶ ላይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጣት ሳቢያ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው መለየት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሃገርን የሚያለማ፣ የሚለውጥና የሚያሳድገው የሰው ሃይል መሆኑን የሚናገሩት ምክትል ቢሮ ኃላፊው እንደ ሃገር የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ይህን ማሳካት አለመቻሉ ከፍተኛ ክፍተት መሆኑን ተናግረዋል፡
በቅድመ መደበኛ ትምህርት ሂደት ላይም ተመሳሳይ የአሰራር ችግሮች እንደነበሩ የተናገሩት አቶ ስዩም ተማሪዎችን ከማሰባሰብ ጀምሮ በዘርፉ የሰለጠኑ መምህራን ሳይኖሩ ፕሮግራሙ እንዲፈጸም ወደ ታች መውረዱ አግባብ እንዳልሆነ ሃላፊዎች ማመናቸውን ገልጸዋል።
የጎልማሶች ትምህርት ፕሮግራም ሃገሪቱን ለማሳደግ ወሳኝ ሂደት ቢሆንም ፤ በአመራሩ አካባቢ ያለው የግንዛቤ ደረጃ ዝቅተኛ መሆን ፕሮግራሙን በቁርጠኝነት ይዞ ለመጓዝ እንቅፋት እንዲፈጠር ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡-
የገዢው መንግስት ባለፉት ሃያ አራት ዓመታት በየጊዜው በሚያወጣቸው አዳዲስ የትምህርት ፖሊሲዎችና ማሻሻያዎች የአማራ ክልል ተማሪዎችን እንደ ሙከራ ማዕከል በማድረግ በትውልዱ ላይ የሚፈጽመው ግፍ አግባብ ባለመሆኑ ይህንን አሰራር ሁሉም የዘርፉ ባለሙያዎችና ህብረተሰቡ በቃ ሊል እንደሚገባው በክልሉ በማገልገል ላይ የሚገኙ የትምህርት ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ለዘጋቢያችን ተናግረዋል፡፡