በአማራ ክልል ከ493 ሺ በላይ ሄክታር መሬት ደን እየወደመነ ተባለ፣ ክልሉ ግን አስተባብሎአል።

ሰኔ ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- በደብረ ማርቆስ የየራባ ደን ፤በአዊ ዞን እንጅባራ የገንብሃ ጫካ ፤በደብረ ታቦር እና በኮምቦልቻም አመታትን ያስቆጠሩ ደኖች እየጠመነጠሩ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል፡፡

ከፍተኛ የደን ቆረጣ በሚካሄድባቸው በአዊ እና በደብረማርቆስ አካባቢዎች ነዋሪዎች ቅሬታቸውን እያሰሙ ነው።

ብዛታቸው ያልታወቀ ጥቁር ዝንጀሮ፣ ጅብ፣ ከርከሮ፣ ድፈርሳ፣ ትልልቅ ጥንቸሎች፣ አረንጓዴ ልባስና ቀይ መንቁር ያላቸው ወፎች፣ የሐበሻ ነብር /Leopard/፣ ከመስከረም እስከ ታኅሳስ ባሉት ወራት ብቻ አኅጉር አቋርጠው የሚመጡ ባለቀለም ወፎችና ለዓይን የሚታክቱ ዓይነታቸውና ብዛታቸው የማይታወቅ ወፎች ደኑን መኖርያ አድረገውት የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ሰአት  በደብረ ማርቆስ ዙሪያ ባለው የደን ቆረጣ የተነሳ እንስሳቱ አንዳንዶችም በሰዎች መኖርያ ቤቶች ውስጥ ዘለው ለመግባት ሲገደዱ ሌሎች ደግሞ ስደትን መርጠዋል።

በአዊ ዞን በገንባሀ ጫካ አካባቢ ሰፍረው የሚገኙ ነዋሪዎች ደግሞ ደኑን አናስቆርጥም በማለት ተቃውሞአቸውን እያሰሙ ነው።
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው  የአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፈለቀ ተሰማ እየተቆረጡ ያሉ ዛፎች ከመጀመሪያውም ለገበያ ተብለው የተተከሉት እንጅ በተፈጥሮ የበቀሉት አይደሉም ብለዋል።

በደብረማርቆስ አካባቢ የጣውላ ስራ የሚሰራ ፋብሪካ መቋቋሙን የገለጹት አቶ ፈለቀ፣ እየተቆረጠ ያለው ሰው ሰራሽ ደን መሆኑን ገልጸዋል።

የአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ በክልሉ ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 70/2002 የተቋቋመ ሲሆን፣ ዛፎችን ቆርጦ የመሸጥ እና የማልማት መብት የተሰጠው ተቋም ነው።