በአማራ ክልል ከመሬት አስተዳደር ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ቅሬታ እየተሰማ ነው፡፡
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 3 ቀን 2010 ዓ/ም ) በአማራ ክልል ከመሬት ልማት እና አስተዳደር ጋር በተያየዘ ከፍተኛ ቅሬታ እየታየ መሆኑን የክልሉ ቅሬታ ሰሚ አቶ ሰይድ ሁሴን አስታወቀዋል፡፡ አቶ ሰይድ በስድስት ወር ሪፖርታቸው አመቱን ሁሉ የቅሬታ ምንጭ ሁኖ ያለው መሬት ነው ብለዋል፡፡ አመቱን ሁሉ ከይዞታ ማረጋገጫ ደብተር አሰጣጥ፣ ካሳ አለመሰጠት እና ፍትሀዊ ያልሆነ አሰራር በዋናነት ህዝቡን ቅር ያሰኙ ጉዳዮች ሆነው ቀጥለዋል ብለዋል፡፡
በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዚገም ወረዳ የመኖሪያ ቤት ግንባታ በማህበር ተደራጅተን መሪ ማዘጋጃ ቤቱ መሥሪያ ቦታ ከፈቀደልን በኋላ ቤት ለመስራት ስንጀምር የወረዳው አካባቢ ጥበቃና መሬት አስተዳደር መሬት አይሰጥም ብሎ ያላግባብ አግዶናል ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡
በዋግ ህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማ ከሰቆጣ ፃግብጅ በሚሰራው መንገድ ምክንያት የእርሻ ማሳቸው የተወሰደባቸው አርሶ አደሮች ተመጣጣኝ ካሳ አልተከፈለንም የሚል ቅሬታ ያላቸው ሲሆን አሁንም ድረስ መፍትሄ እንዳላገኙ አመላክተዋል፡፡
በደሴ ከተማ አስተዳደር ፒያሳ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ቦታው ለመልሶ ማልማት ስለተፈለገ የምንኖርበት ቤትና ለንግድ የምንሰራበት ድርጅት በመፍረሱ ምክንያት ምትክ ቦታ ሳይሰጠን ከአካባቢው ልቀቁ ተባልን የሚሉ ቅሬታዎች እየቀረቡ ነው።
በደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር እብናት ወረዳ የውስጥ ለውስጥ መንገድን ለመስራት ቤታችን በመፍረሱ ለቦታችን ትክ አልተሰጠንም በማለት ቅሬታቸውን ያሳመሉ።
በተመሳሳይ በደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር ላይ ጋይንት ወረዳ የወል መሬት በግለሰቦች እየታረሰ በመሆኑ ለሚመለከተው ክፍል ቢያመለክትም ሰሚ አጥተዋል።
በጎንደር ከተማ አስተዳደር የይዞታ ቦታ ተጣርቶ እንዲፀድቅልን በተደጋጋሚ ብንጠይቅም ምላሽ አጣን ሲሉ ነዋሪዎች ቅሬታዎችን እያቀረቡ ነው፡፡ በምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር አዋበል ወረዳ ካዳስተር በሚሰራባቸው ቀበሌዎች መሬታችንን ግጦሽ ነው በማለት ተወሰደብን በማለት ከ100 የሚበልጡ አርሶ አደሮች ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው።
በደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር ተሁለደሬ ወረዳ በመሬት አስተዳደር የፍርድ ቤት ትዕዛዞች በመብዛታቸው የሰራተኛውም ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ተገልጋዮች ተንገላታን ሲሉ፣ በመቅደላ ወረዳ ደግሞ የማህበር ቦታ የተሰጠው በእጣ በመሆኑ እጣ ያልወጣላቸው ዜጎች አሁንም ቤት አልባ ሁነዋል።
በመሃል ሳይንት ወረዳ በመሬታችን ላይ መንግስት ለህብረተሰቡ ውሃ ገንብቶ ካሳ አልሰጠንም ያሉ ነዋሪዎች ቅሬታ ወደ ብጥብጥ ያመራ ሲሆን፣ በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ደግሞ በላይ ዘለቀ ክፍለ ከተማ የይዞታ ቦታን በተመለከተ አጥር ለማጠር እና እድሳት ለማደስ እንዲፈቀድልን ብንጠይቅም ምላሽ አጣን ሲሉ ነዋሪዎች ተናግረዋል ፡፡ 36 ሺ የሚሆኑ ቤት ፈላጊዎች ላለፉት አራት አመታት በባንክ አስከ 90 ሽህ ብር በመቆጠብ በከተማ አሰተዳደሩ 3 ቢሊዮን 24 ሚሊዮን ብር በድምር ያስያዙ ቢሆንም፣ መፍትሄ ሳያገኙ ገንዘባቸው በዝግ አካውንት እንደተቆለፈ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ፌድራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የስኳር ኮርፖሬሽን የበለስ ስኳር ልማት ሰራተኞች ህገ መንግስታዊ መብታችን ተጥሶ በክልሉ ርዕሰ መሰተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና የአዋ ብሄረሰብ አሰተዳደር ዞን የሰጠንን የቤት መስሪያ ቦታ የማግኝት መብታችን በመነፈጉ የጃዊ ወራዳ ፈንዲቃ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ባዶ ቦታ የለኝም በሚል ቤት አልባ አድርጎናል ሲሉ ክስ አሰምተዋል።
በአሁኑ ስዓት በመላ ሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ ቅሬታ እየፈጠረ ያለው የመሬት ችግር ሲሆን፣ በዘርፉ በሚታየው የመሬት አመራር እና የገጠር ወጣቶች መሬት አልባ በመሆናቸው በከፍተኛ ሁኔታ ለስደት እየተዳረጉ እንደሚገኙ ከዚህ በፊት የወጡት ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡