በአማራ ክልል በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች አብድራፊ ወደ ትግራይ ክልል ሊካተት ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገለጹ

መስከረም ፳፮(ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከአሁን ቀደም  ከትርፍ አምራች የአማራ ክልል ወረዳዎች ወደ ትግራይ ክልል የተካለሉ ቦታዎች አሁም ድረስ በሁለቱ ክልሎች መካከል የውዝግብ ምክንያት ሆኖ በቀጠለበት በዚህ ወቅት የአብደራፊ ከተማን

ወደ ትግራይ ክልል ለመጠቅለል የሚደረገው ቅድመ ዝግጅት ስጋት አሳድሮብናል ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

የክልሉ መሪዎች  ለአጎራባች ክልል ኢንቨስተሮችና ከፍተኛ ባለስልጣናት የሚሆኑ የእርሻ መሬቶችን በገጸ በረከትነት ለመስጠት መሯሯጣቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ለክልሉ ርእሰ መስተዳድር ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና ለሌሎች ከፍተኛ አመራሮች

ተናግረዋል፡፡ አንድ ተናጋሪ አብደራፊ ወደ ክልል አንድ  ትሄዳልች ’ የሚለው ወሬ በስፋት መሰራጨቱ በህዝቡ ውስጥ ስጋት መፍጠሩን ጠቁመው ፣ በአሁኑ ሰአት የሚታየው የመንገድ ግንባታ ይህንን ያጠናክራል ብለዋል።

ተናጋሪው አክለውም በ ሰሮቃ ከተማ አካባቢ በትግራይና በአማራ ክልል ነዋሪዎች መካከል  በየጊዜው ግጭት እየተከሰተ ጉዳት ቢደርስም፣ የሁለቱ ክልሎች ባለስልጣናት ግጭቶችን በየጊዜው ችላ በማለታቸው  ወደ ባሰ ውስብስብ ነገር እየገባን ነው ብለዋል።

ሌላ ቅሬታ አቅራቢ ደግሞ በአካባቢው የሚታየው የመንገድ አሰራር አብድራፊን ሆን ብሎ ከአማራ ክልሎች እንዳትገናኝ በማድረግ ከቆይታ በኋላ ወደ ትግራይ ክልል  ለመጠቅለል እየተሰራ ያለ ስራ መኖሩን ይጠቁማል ይላሉ።

“ቀደም ብላችሁ በመምጣት ልትጎበኙን ይገባ ነበር “በማለት በምርጫ ወቅት የሚደረግ የተለመደ ጉብኝት መሆኑን ነካ አድርገው ያለፉት ሌለው ተናጋሪ፣ በአካባቢው በሚከሰቱ ችግሮች ዙሪያ የወረዳ አመራሮች መፍትሄ የማይሰጡት በበላይ አመራሮች በሚደርስባቸው

ተጽዕኖ የተነሳ ነው ይብለዋል፡፡ ተናጋሪው “ከማይካድራ የተነሳው መንገድ አብርሃጅራ በመግባት አብደራፊን ማግኘት እያለበት አብደራፊን ሳይገባ ተጠምዝዞ ወደ ክልል አንድ ዳንሻ የተመለሰው መንገድ በምን ምክንያት  ነው ?” የሚል ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣   “አብደራፊ

ወደ ክልል አንድ ትሄዳለች ወይስ አትሄድም? ቁርጥ ያለ መልስ ዛሬውኑ ንገሩን  በማለት  አመራሮችን አፋጠዋል፡፡ ከተለያየ አቅጣጫ የቀረቡትን የአብደራፊን ዕጣ ፈንታ የተመለከቱትን ጥያቄዎች በተመለከተ የክልሉ መሪ የተብራራ መልስ ባለመስጠታቸው ተሰብሳቢው

ቅሬታውን ገልጿል፡፡ የምእራብ አርማጮሆ ህዝብ ለሚያቀርባቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መልስ እንደማያገኝ አንድ አስተያየት ሰጪ   የሃገር ሽማግሌ ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው ብሄር ተኮር የፌደራል ስርአት በክልሎች መካከል የድንበር ውዝግብ እንዲነሳ ማድረጉን ታዛቢዎች ይገልጻሉ። በአማራ እና በትግራይ ፣ በትግራይና በአፋር፣ በአማራና በኦሮምያ፣ በኦሮምያና በደቡብ፣ በኦሮምያና በሶማሊ፣ በጋምቤላና

በደቡብ ክልሎች መካከል ያልተፈቱ የድንበር ውዝግቦች አሉ ። ኢህአዴግ በበኩሉ  የፌደራል ስርአቱ የብሄር ግጭቶች እንዲቀንሱ አድርጓል በማለት ይከራከራል።