ሚያዝያ ፲፮ (አሥራ ስድስት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የክልሉ ወኪላችን የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽን መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ እና ፖሊሶች በየቀኑ የሚለዋወጡ የስልክ መረጃዎችን ተንተርሳ ባጠናቀረችው መረጃ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ከመልካም አስተዳደር እጦት፣ ከፍትህ መጓደል፣ ከመሬት ጋር በሚነሳ አምባጓሮ ፣ ድህነትና ስራ አጥነት ፣ ሙስናና ተዛማጅ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ አለመግባባቶች እንዲሁም ፖሊሶችና ወታደሮች በሚወስዱዋቸው እርምጃዎች ከሰኞ እስከ ሃሙስ በአሉት ቀናት በእየቀኑ በአማካኝ አምስት፣ ከአርብ እስከ ቅዳሜ ባሉት ቀናት ደግሞ በየቀኑ 11 ሰዎች ህይወታቸውን ያጣሉ። ይህ አሃዝ በትራፊክ አደጋ የሚሞቱትን ዜጎች ቁጥር አያካትትም። እንዲሁም በአብዛኛው የገጠሪቱ አካባቢዎች የሚደርሱ ግድያዎች ሪፖርት የማይደረግባቸው በመሆኑና አሃዙ በአብዛኛው በወረዳ ከተሞች ያለውን እለታዊ ሁኔታ የሚያመለክት በመሆኑ የሟቾች ቁጥር ከተጠቀሰው አሃዝ በብዙ እጅ ሊልቅ እንደሚችል ዘጋቢያችን ትገልጻለች።
በወር ውስጥ በአማካኝ ከ200 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን የሚያጡ ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥር ከመቀነስ ይልቅ ከወር ወር እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑን መረጃዎች ዋቢ በማድረግ ገልጻለች።
ላለፉት ሁለት ወራት በተደረገው ምርመራ፣ በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ አገዛዝ፣ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን የህወይት መጥፋት ለመከላከል ምንም አይነት እርምጃ ሲወስድ አልታየም። እንደ ትራፊክ አደጋ ሁሉ ከፍትህ እጦት ጋር በተያያዘ የሚደርሱት ግድያዎችም መረሳታቸውን የምትገልጸው ዛጋቢያችን፣አብዛኞቹ ግድያዎች ከፍትህ እጦት፣ ከእርሻ መሬት ጥበት፣ ከስራ አጥነትና ድህነትና ከአስተዳደር መጓደል ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ መሆናቸው ፣ አገሪቱ ያለችበትን ችግር ያሳያል ትላለች።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እና የአስተዳደር እና ፀጥታ ጉዳዩች ቢሮ በ1999 እና በ2007 ዓ/ም በአማራ ክልል የነፍስ ግድያ ወንጀል መንስኤ የሆኑ ጉዳዮች በሚል በጋራ ባስጠኑት የዳሰሳ ጥናት ላይ ከ1995-1999 እና ከ2000-2007 ዓ/ም ድረስ ባሉት ሁለት አምስት ዓመታት ውስጥ በክልሉ የተፈፀሙ የነፍስ ግድያ ወንጀሎች አብዛኛዎቹ በፍትህ አለመርካት እና በመሬትና ከመሬት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች የተከሰቱ መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡
ችግሩ ከቤተሰብ አልፎ የህብረተሰቡና የአገር ጭምር መሆኑን ጥናቱ ያመለክታል። በእነዚህ አካባቢዎች በአንድ አመት ውስጥ ለፖሊስ ሪፖርት የደረሱ የ2005-2008 ዓ.ም እና የ2009 የስድስት ወራት ግብረ መልሶች እንደሚያሳዩት 26 ሺ 128 ሰዎች በሞት፣ 22 ሺ 286 ሰዎች ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።